ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን ለማጠናከር በትኩረት መስራቷን ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን ለማጠናከር በትኩረት መስራቷን ትቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን ለማሳደግ የምታከናውናቸውን ተግባራት አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለፁ።
የኢትዮጵያን ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ልማት በትኩረት እየሰራች ትገኛለች።
ባለፉት ዓመታት የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሶስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደስራ ማስገባት መቻሉን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት በስፋት መስራቷ በዘርፉ ተጠቃሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን ያስቻላት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ ከታዳሽና ንፁህ ኃይል የሚገኝ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ተቋም ውስጥ በግንባር ቀደምነት እየሰራች መሆኗን አንስተው፤ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን ለማጎልበት የምታከናውነውን ተግባር አጠናክራ መቀጠሏንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ኃይል ከምታቀርብላቸው ከጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ በተጨማሪ ወደ ታንዛኒያ የኃይል ሽያጭ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ከሌሎች ሀገራት ጋርም በኃይል ለመተሳሰር ጥናት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገራት የምታቀርበው ከምታመነጨው ኃይል አስር በመቶ ያነሰ እንደሆነ በመግለጽ፤ የሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት የምታቀርበውን ኃይል በማቀናጀት በታዳሽ ኃይል ቀዳሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ግዙፍ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
16 የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ፕሮጀክቶችም በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ተቋሙ የኢትዮጵያን ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።