ቀጥታ፡

በክልሉ ሳምንቱን ሙሉ ምርት የሚያቀርቡ የግብይት ማዕከላትን በማቋቋም ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት እየቀረበ ነው 

ሆሳዕና፤ ግንቦት 29/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ በተቋቋሙ የግብይት ማእከላት ከእሁድ እስከ እሁድ ምርቶች እየቀረቡ እንደሚገኝ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ምክትልና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደስታ ዶሌቦ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በክልሉ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ምርቶችን በግብይት ማዕከላት በስፋት የማቅረብ ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በዚህም በክልሉ ከ140 በላይ ከእሁድ እስከ እሁድ ምርት የሚቀርብባቸው የግብይት ማዕከላትን በማቋቋም ለማህበረሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
 


 

ቢሮው በክልሉ 5 ከተሞች ዘመናዊ የግብይት ማዕከላት ማስገንባቱንና የወራቤ ከተማ ዘመናዊ የግብይት ማዕከል ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አስታውሰዋል።

የግብይት ማዕከሉ አምራችና ሸማቹን ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ማስቻሉን ገልጸዋል።

የስልጤ ዞን ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ሽታ መሀመድ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም የሚያመርቱትን ምርት በቀላሉ ለማህበረሰቡ ለማቅረብ የሚያስችል የግብይት ማዕከል ባለመኖሩ ገበያ ወዳለበት ስፍራ ይጓዙ እንደነበር ተናግረዋል።
 


 

በወራቤ ከተማ ተገንብቶ የተጠናቀቀው ዘመናዊ የግብይት ማዕከል የሚያመርቱትን ምርት ለማህበረሰቡ በቀላሉ ለማቅረብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። 

በከተማው ስራ የጀመረው የግብይት ማዕከል የሚፈልጉትን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የወራቤ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሳድያ ጀማል ናቸው።
 


 

በከተማው ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው ዘመናዊ የግብይት ማዕከል ምርትን በጥራትና በፈለጉት ጊዜ ለማግኘት ማስቻሉን ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በቅርቡ በወራቤ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትንና ዘመናዊ የግብይት ማዕከልን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም