ቀጥታ፡

በዞኑ አርሶ አደሮች የቆላ ፍራፍሬን በኩታ ገጠም በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው

ገንዳ ውሃ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን የቆላ ፍራፍሬን በኩታ ገጠም በማልማት የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እያደገ መሆኑን  የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የመስኖና ውኃ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ አስናቀው አራጋው እንደገለጹት፤ በዞኑ ለአካባቢው ሥነ-ምሕዳርና የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የሙዝ፣ የማንጎ፣ የፓፓያና የዘይቱን ፍራፍሬዎች በኩታ ገጠም ዘዴ እየለሙ ይገኛሉ።

ይህንን ተግባር ይበልጥ በማስቀጠልም በመጪው ክረምት 200 ሄክታር መሬት በመተማና በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች በኩታ ገጠም ለማልማት የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 

ለተከላው የሚያስፈልጉ የቆላ ፍራፍሬ ችግኞችም በበጋው ወራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የፍራፍሬ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ የባለሙያ ድጋፍና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ፣ የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ እንደሚገኝም አቶ አስናቀው አስገንዝበዋል።

ቀደም ሲል የተተከሉ የፍራፍሬ ምርቶች የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከመደገፍ ባለፈ፣ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ሀብት ማፍራት ማስቻላቸውንም ገልጸዋል።

በዞኑ መተማ ወረዳ ወዲ ገምዞ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሲሳይ ይመር በበኩላቸው፤ ለአካባቢው ሥነ-ምሕዳር ተስማሚ የሆኑ የቆላ ፍራፍሬዎችን በማልማት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።

ካለፉት ዓመታት ያገኙትን ልምድ በመጠቀምም በመጪው ክረምት ልማቱን ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ጋር በማስተሳሰር፣ የቆላ ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሌላው የዞኑ የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ታርቆ አያሌው በበኩላቸው፤ ፍራፍሬን በተበታተነ ማሳ ከመትከል ይልቅ በኩታ ገጠም ማልማት ግብዓትን፣ ቴክኖሎጂንና ጉልበትን በጋራ በመጠቀም ምርታማ ለመሆን ያግዛል ብለዋል። 

ከዚህ በፊትም በሙዝ ልማት የተሳተፉ መሆናቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፣ አሁን ደግሞ በስፋት በማልማት የገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግ እየሠሩ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ባለፉት ዓመታት ከ1 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በቆላ ፍራፍሬ የለማ መሆኑን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም