ቀጥታ፡

ሚሊሻ የሀገርና የሕዝብ ጥሪ ሲመጣ ማረሻውን ከቀዬው አኑሮ፣ መሣሪያውን በትከሻው አድርጎ ወደ ግንባር የሚተም የቁርጥ ቀን የሕሊና ወታደር ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2018(ኢዜአ)፦ ሚሊሻ የሀገርና የሕዝብ ጥሪ ሲመጣ ማረሻውን ከቀዬው አኑሮ፣ መሣሪያውን በትከሻው አድርጎ ወደ ግንባር የሚተም የቁርጥ ቀን የሕሊና ወታደር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን 30ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተናል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ሚሊሻ፣ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም ለማስከበር ታላቅ መሥዋዕትነት የከፈለ ሕዝባዊ ኃይል ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ይህ ኃይል ልዩ የሚያደርገው ካለበት ማኅበረሰብ የወጣ፣ አብሮ የሚያርስና የሚያመርት፣ ሀገርና ክልል በገጠሟቸው ፈተናዎች ሁሉ ግንባር ቀደም በመሆን መሥዋዕትነትን በመክፈል ለሀገር ትልቅ አስተዋጽዖን አበርክቷል ብለዋል።

ሀገራችንና ክልላችን ከተለዋዋጭና ውስብስብ የፀጥታ ተግዳሮቶች ጋር እየተጋፈጡ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ተቋማዊ አቅምን መገንባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም፤ መንግሥታችን የሚሊሻውን ኃይል አደረጃጀት ዘመናዊ ለማድረግ፣ በዕውቀትና በሥልጠና ለማበልጸግ፣ በቴክኖሎጂ ለማዘመን እንዲሁም ትጥቅና አቅርቦቱን ለማሻሻል የጀመረውን ተቋማዊ የሪፎርም ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክትም ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ሲሉ ሕይወታቸውን ለሰጡ ጀግኖቻችን ታላቅ አክብሮትና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም