የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዘመኑን በሚመጥን አደረጃጀትና በላቀ ብቃት የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር እየጠበቀ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዘመኑን በሚመጥን አደረጃጀትና በላቀ ብቃት የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር እየጠበቀ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
ድሬዳዋ፤ ግንቦት 29/2018(ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዘመኑን በሚመጥን አደረጃጀትና በላቀ ብቃት የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር እየጠበቀ መሆኑን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
የሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን የ27ኛ ዙር ፅናት ኮርስ ዕጩ መኮንኖች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ሠራዊቱ ዘመኑን በሚመጥን አደረጃጀትና ብቃት በመታገዝ የሀገር ሉዓላዊነትና ክብርን እየጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ሉዓላዊነቷንና ክብሯን አስጠብቀው ያስረከቡን የጀግኖች ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ በዚህ ወቅትም ሠራዊቱ የላቀ ብቃቱን በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል ብለዋል።
ሠራዊቱ ከውጭ ጠላቶች ተልዕኮ ተቀብለው ሀገር የሚበድሉ ባንዳዎች እና ተላላኪዎችን የጥፋት ተልዕኮ እያመከነና ተከታተሎ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ገልፀዋል።
የዛሬ ተመራቂዎችም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን በመመከት በጀግንነት መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ተመራቂዎቹ ያገኟቸውን ዘመናዊ ወታደራዊ ዕውቀት ካላቸው ተሞክሮ ጋር በማቀናጀት የሠራዊቱን ተልዕኮ አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የሁርሶ ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ከድር ጫንጮ በበኩላቸው፤ ታሪካዊው ትምህርት ቤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር በታላቅ መስዋዕትነት የሚጠብቁ ጀግኖችን ማፍራቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ተመራቂዎቹ በአካል ብቃት፣ በአመለካከት፣ በሥነ-ልቦና እና በሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ሥልጠና የወሰዱ በመሆናቸው፣ የትኛውንም ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተመራቂ መኮንኖቹ በበኩላቸው፤ በቀሰሙት ወታደራዊ ዕውቀትና ጥበብ ታግዘው የሀገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በማናቸውም ፈተና ውስጥ ሆነው የዜጎችን ደህንነት፣ የሀገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለመጠበቅም ቃል ገብተዋል።
በመርሃ ግብሩ በመከላከያ ሚኒስቴር የትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄነራል ይመር መኮንን በሥልጠና ቆይታቸው የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዕጩ መኮንኖች ማዕረግ አልብሰዋል።
በምረቃው የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ እንዲሁም ሌሎች ሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ፣ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ እንዲሁም ኡጋዞችና አባገዳዎች ተገኝተዋል።