ቀጥታ፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተነድፈው ተግባራዊ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ለአካባቢ ጥበቃ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2018(ኢዜአ)፦ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማቶችን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተነድፈው የተተገበሩ ፕሮጀክቶች ለአካባቢ ጥበቃ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ።

የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ53ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ ተከብሯል።

ቀኑን ምክንያት በማድረግም ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ከተማ የተውጣጡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የስራ ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ የተሰራውን የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ፕሮጀክቱ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቆ ክፍት መደረጉ ይታወሳል።


 

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተነድፈው የተተገበሩ ፕሮጀክቶች የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።

በአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው፤ ይህም የአየር ብክለት መቀነስን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች እያስገኘ ነው ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲቸራት ያስቻለ መሆኑን በመጠቆም፤ ሥነ ምህዳርን በማሻሻል በኩል ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት አካባቢ ጥበቃን ውጤታማ እያደረጉ ካሉ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

በፕሮጀክቱ ሀገር በቀል ዛፎች መተከላቸውን ጠቅሰው፤ ሀገር በቀል የኮንሶ የአካባቢ ጥበቃ እውቀቶች አሻራ ያረፈበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም አንስተዋል።

መሰል የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራዎች ኢትዮጵያ ተምሳሌታዊና ተጠቃሽ ሀገር እያደረጋት ነው ሲሉም ዋና ዳይሬክተሯ አመላከተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እሸቱ ለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የእግረኛ መንገዶች፣የሳይክልና አማራጭ መንገዶችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ይህም በተሽከርካሪዎች ወደ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ እንዲቀንስ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል። 

ፕሮጀክቱ ከሕዝቡ ጋር በመሆን ለውጤት በቅቷል ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቱ በሚጠበቀው ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ ሕዝቡ ሊንከባከበው ይገባል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶኤ (ዶ/ር)፤ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያዊያን አቅም በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለውጤት መብቃቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል።      


 

 ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ላላት ቁርጠኝነት መሰል የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ምስክሮች ናቸው ያሉት ተወካዩ ተፈጥሮን ከዘመናዊነት ጋር አጣጥሞ መሄድ ያለውን ውጤት አመላካች ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም