አነስተኛ እና መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት በተጨባጭ እየቀነሱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አነስተኛ እና መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት በተጨባጭ እየቀነሱ ነው
መቱ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የተገነቡ አነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች፣ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚያጋጥመውን የውሃ እጥረትና ድርቅ ለመቋቋም የሚያስችል አቅም እየፈጠሩ መሆኑን የክልሉ የመስኖና አርብቶ አደሮች ልማት ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በውሃ እጥረት ምክንያት በሰዎችና በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን የድርቅ ጉዳት ለመቋቋም 'ፊና' የተሰኘ ፕሮጀክት እየተተገበረ ይገኛል።
በፕሮጀክቱ አማካኝነት 73 አነስተኛ እና መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ከእነዚህም ውስጥ የ40ዎቹ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል።
በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ዘንድ እየተተገበሩ ያሉት እነዚህ የ“ፊና” ፕሮጀክቶች፣ የድርቅ አደጋን የመቋቋም አቅምን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።
በተለይም በቦረና፣ በሐረርጌና በባሌ ዞኖች በአርብቶ አደር አካባቢዎች በድርቅ ምክንያት በሰዎችና በእንስሳት ላይ ይከሰት የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ እገዛ ማድረጋቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቶቹ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከድርቅ ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ እየታደጉ መሆኑንም አንስተው በቀጣይም ልምዱን ሌሎች የውሃ እጥረት ወደሚያጋጥማቸው አካባቢዎች በማስፋፋት፣ ሊከሰት የሚችለውን ችግር አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቋቋም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
እነዚህ የመስኖ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀው ወደ አገልግሎት ሲገቡ የአካባቢውን የውሃ እጥረት በዘላቂነት ከመቅረፍ ባለፈ በአርብቶ አደሩ ዘንድ በከብት እርባታ ላይ ብቻ የተደገፈውን ህይወት፣ ከግብርና ልማት ስራዎች ጋር በማስተሳሰር ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል ።