ቀጥታ፡

ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ለዘንድሮው 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ስኬት ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ገለፁ።

የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከሰኔ 24 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 17 ቀን የ2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥም ተገልጿል። 

የአገልግሎቱን ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመስጠት አገልግሎቱ እያደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተከናውኗል ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ560 ሺህ በላይ ተፈታኞች ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በበይነ-መረብ  እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

ለዚህም ተማሪዎች በቂ የኮምፒውተር ልምምድ የሚያደርጉበት አሰራር መዘርጋቱን አመላክተው፤ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ውስንነት ባሉባቸው አካባቢዎች ፈተናው በወረቀት እንደሚሰጥም ገልፀዋል።

በተጨማሪም ተፈታኞች ፈተናውን በፍትሐዊ መልኩ እንዲወስዱ ለማድረግ አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ሀገር አቀፍ ፈተናውን ለሚወስዱ አካል ጉዳተኞች ምቹ የመፈተኛ ከባቢን ለመፍጠርና እንደ አካል ጉዳት አይነታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የፈተና ሂደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢንተርኔት እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።

ተፈታኝ ተማሪዎች ያላቸውን ቀሪ ጊዜ በመጠቀም ለፈተና ዝግጁ የሚያደርጋቸውን እንዲሁም የስነልቦና ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም