በክልሉ ዘመናዊ የግብር አሰባሰብን ተግባራዊ በማድረግ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘመናዊ የግብር አሰባሰብን ተግባራዊ በማድረግ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ትኩረት ተደርጓል
ባህር ዳር ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ዘመናዊ የግብር አሰባሰብን ተግባራዊ በማድረግ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ትኩረት መደረጉ ተገለፀ።
በክልሉ ውስጥ የገቢ አቅምን በማሳደግ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።
የገቢ የመሰብሰብ አቅሙን ለማሳደግም የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን እንደተቻለ ተመላክቷል።
በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ የመሰብሰብ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የህግ ተገዥነትን በማሳደግና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዚህ በጀት ዓመት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
እስከ ግንቦት 20/2018 ዓ.ም ድረስ በተቀናጀ መንገድ በተሰበሰበ ገቢም የዕቅዱን ከ73 በመቶ በላይ ማከናወን እንደተቻለ አመልክተዋል።
የተሰበሰበው ገቢም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ28 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።
ተጨማሪ ገቢው የተገኘው ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከርና በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትልና ቁጥጥር በመደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
እንዲሁም ከዚህ ቀደም በግብር ስርዓቱ ውስጥ ያልነበሩ ግብር ከፋዮችን ወደ ግብር ስርዓቱ ማስገባት በመቻሉ መሆኑንም አክለዋል።
በሌላ በኩል በ259 የታክስ ማዕከላት የተቀናጀ የመንግስት የግብር አስተዳደር ስርዓት ተደራሽነትን በማሳደግ የተሟላ አገልግሎት ማቅረብ እንደተቻለ አመልክተዋል።
በግብር አሰባሰብ ሂደቱ ቅሬታ ላቀረቡ 46 ሺህ 285 ግብር ከፋዮች ያቀረቡትን ቅሬታ በመመርመር አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት መቻሉንም ገልፀዋል።
በተቋሙ ውስጥ የስነ ምግባር መጓደል የተስተዋለባቸው ባለሙያዎች ላይ ከስራ እስከ ማሰናበት የሚያደርስ ቅጣት መወሰኑን አብራርተዋል።
በቀጣይም የግብር አሰባሰብ አሰራሩን በማዘመን ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ርብርብ ይደረጋል ነው ያሉት።