ህዝቡ ለሰላም ያለው ፅኑ አቋም የጽንፈኛ ቡድኖችን የተቀናጀ ምርጫ የማደናቀፍ ጥረት አክሽፏል - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ ለሰላም ያለው ፅኑ አቋም የጽንፈኛ ቡድኖችን የተቀናጀ ምርጫ የማደናቀፍ ጥረት አክሽፏል
ባህር ዳር፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ ህዝቡ ለሰላም ባለው ፅኑ አቋም የጽንፈኛ ቡድኖችን የተቀናጀ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ የማደናቀፍ ጥረት ሙሉ በሙሉ ማክሸፉን የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ ገለፁ።
የሰላም ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ በሸኔ የሽብር ቡድን የደረሰው ጥቃት የሚወገዝ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ የበላይነት እንዲረጋገጥና የፀና መንግስትና ሀገር እንዲኖር ምርጫ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
በዚህም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በታሪክ ሊጠቀስ በሚችል አግባብ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የተሳተፈበትን ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ ተችሏል ብለዋል።
ምርጫው በሁሉም መለኪያዎች በውጭ ታዛቢዎች ጭምር የተረጋገጠ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ሊከናወን መቻሉን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ ፅንፈኛ ቡድኖች ያለ የሌለ አቅማቸውን ተጠቅመው ምርጫውን ለማደናቀፍ ያደረጉትን የተቀናጀ ጥረት ሰላም ወዳዱ ህዝብ ሂደቱን ሰላማዊ በማድረግ ሴራቸውን አክሽፎታል ሲሉም ተናግረዋል።
የባዕዳን ሴራ ተሸካሚ የሆኑ ፅንፈኛ ቡድኖች ከምርጫ በፊት ህዝብ ካርድ እንዳያወጣ፣ የድጋፍ ሰልፍ እንዳይወጣና በምርጫው ዕለት ድምፅ እንዳይሰጥ የተቀናጀ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም በሀገሩ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ህዝብ ማስፈራሪያና ዛቻቸውን ብሎም የጥቃት ሙከራዎችን ተቋቁሞ ምርጫውን በማካሄድ ሴራቸውን በማክሸፍ የዲሞክራሲ የበላይነት እንዲረጋገጥ ማድረጉን አብራርተዋል።
በምርጫው ሴራቸው የከሸፈባቸው ፅንፈኞች አሁንም ሌላ የጥፋት ካርድ በመምዘዝ የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ ህብረትና መተሳሰብ በማይመጥን መንገድ ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል ጥቃት መፈፀማቸውን ገልፀዋል።
የሸኔ የሽብር ቡድን ከሰሞኑ በአርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ጥቃት ማድረሱን አንስተው፤ ድርጊቱ በሁሉም ዘንድ መወገዝ ያለበትና ዳግም እንዳይከሰት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
ሆኖም አሳሳች ምስሎችን ጭምር በመጠቀም ችግሩን ለማባባስ በሴረኞች የተደረገው ጥረት በህዝቡ አስተዋይነት እና ሰላም ወዳድነት ሊከሽፍ መቻሉን ገልጸዋል።
የህብረተሰቡን፣ የሃይማኖት ተቋማትን ብሎም በአማኞች መካከል ለዘመናት የተገነባውን የአብሮነት እሴት በማፍረስ ግጭት ለመቀስቀስ የተሄደበት ርቀት የሚወገዝ መሆኑን አንስተዋል።
ጉዳዩ እንዳይራገብ ያደረጉ የመንፈሳዊ ማህበራት ወጣቶችን ያመሰገኑት ሚኒስትሩ በቀጣይ ችግሩን በማባባስ ሀገርና ህዝብን አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረገውን ሴራ ሁሉም ሊከላከለው እንደሚገባም አሳስበዋል።
ህዝቡ የጽንፈኞችን ምርጫን የማደናቀፍ ሴራ እንዳከሸፈው ሁሉ አብሮነትን በማጠናከር ሀገር የመገንባትና የማፅናት ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አስገንዝበዋል።