ቀጥታ፡

የወጣቶች ንቁ የምርጫ ተሳትፎ የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ትልቅ አቅም ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2018(ኢዜአ)፦ ወጣቶች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያደረጉት ንቁ ተሳትፎ ኢትዮጵያን በጽኑ የዴሞክራሲ መሰረት ላይ ለመገንባት የሚችሉበትን ትልቅ አቅምና እድል የፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።

ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል በዚህም ኢትዮጵያውያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያም አሸንፋለች።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ተወካይ አሌክስአንደር ንጉሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፌዴሬሽኑ በምርጫው ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶችን በታዛቢነትና በመራጮች ትምህርት መስጠት ሂደት በማሳተፍ ሀላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም በምርጫው በሀገር አቀፍ ደረጃ 32 ሺህ 500 ወጣቶች በታዛቢነት፣ በአስተባባሪነት ደግሞ 2 ሺህ 500 ወጣቶችን በማሰማራት መሳተፉንና ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በሂደቱ የፌዴሬሽኑ ታዛቢዎች ከተለያዩ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተወካዮች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ከምርጫ አስፈፃሚዎች ጋር በቅንጅት በመስራት ሀላፊነቱን በብቃት መወጣቱን ገልፀዋል።

በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫም ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው የነገዋን ኢትዮጵያ መገንባት የሚችሉበትን አቅምና ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምርጫው በኢትዮጵያ የተረጋጋ ፖለቲካና የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ጥሩ መሰረት እየያዘ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ይህም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጭው ትውልድ ለማስረከብ ትልቅ አድል የፈጠረ መሆኑን ጨምረው አንስተዋል፡፡

በተለይም በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቶች በፖለቲካው ተሳትፎ እንዲያደርጉ እድል የሰጡበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም