ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ድል ነው - ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ድል ነው - ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ
ባህር ዳር፤ ግንቦት 29/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በታላቅ ድል የሚታይ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ አስታወቁ።
ምርጫውን ለማደናቀፍ የተደረጉ በርካታ ሙከራዎችን በማክሸፍ ስኬታማ ምርጫ ማካሄድ መቻሉንም ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ምርጫውን ለማደናቀፍ የተደረጉ የተለያዩ የጥፋት ሙከራዎች በሙሉ ከሽፈው የተሳካ ምርጫ መካሄዱን አንስተዋል።
በታሪካቸው ከትጥቅ ትግል ውጪ የምርጫ ኮሮጆን የማያውቁ የኢትዮጵያ ጠላቶችን የጥፋት አጀንዳ ተቀብለው በህዝብ ላይ ስጋትን ለመፍጠር ሁሌ የሚውተረተሩ አካላት ምርጫውን ለማደናቀፍ ሙከራ እድርገዋል ብለዋል።
እነዚህ ተገዢ ባንዳዎች በመቀናጀት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዳይካሄድ ለማድረግ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅት እና ከምርጫ በኋላ የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገዋ ሲሉ ገልጸዋል።
ሆኖም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት መድረክ መሆኑንም አክለዋል።
በተለይም ጽንፈኛ ቡድኖች ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ የተዛቡ መረጃዎችን ሲያሰራጩ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በምርጫው ሰሞንም የሽብር ድርጊቶችን ጭምር ለመፈጸም መሞከራቸውን አንስተዋል።
ለአብነትም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኳስ እየተመለከቱ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ቦምብ በመወርወር የአንድ ተማሪ ሕይወት እንዲያልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ በሌሎች ተማሪዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ አድርሰዋል ብለዋል።
ጽንፈኞች የምርጫውን ዕለት ጨምሮ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ያደረጉ ቢሆንም ሙከራው ሳይሳካ ቀርቷል ያሉት ሚኒስትሩ ይህ አልሳካ ያላቸው የጥፋት ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ በዜጎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ገልጸዋል።
በጥቃቱም በጸጥታ አካላት፣ በቤተ እምነት፣ በመኖሪያ ቤቶች እና በመሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን በተመሳሳይም በዞኑ ሀንቀሎ ዋቤ እና በሺርካ ወረዳዎች ተመሳሳይ ችግሮች መፍጠራቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ሂደትም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች፣ ከኦሮሚያ ክልል አመራሮች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ የተፈጠረውን ችግር ላልተገባ የፖለቲካ ጥቅም ለማዋል የሚደረገው ሙከራ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለውም ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ሁኔታውን መነሻ በማድረግ የራስን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሟላት የሚሯሯጡ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበው፣ ጥፋተኛውን አካል በጋራ ማውገዝ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በአጠቃላይ፣ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ በተለያዩ መንገዶች የሚገለጹ ሙከራዎች የነበሩ ቢሆንም፣ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል ብለዋል።