ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ 19ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር ነገ ግንቦት 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውድድሩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

መነሻው እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው ውድድር ላይ በወንዶች 455፣ በሴቶች ደግሞ 183 በድምሩ 638 አትሌቶች እንደሚሳተፉ በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን የውድድሩ ዋና አላማ በስዊድን ለሚካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድሩ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች መምረጥ እና ተተኪዎች ማፍራት ነው ብለዋል።

የፌዴሬሽኑ ውድድር እና ተሳትፎ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ጊዜ አድነው በበኩላቸው በውድድሩ ላይ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ አትሌቶች የገንዘብ፣ የሜዳልያና የዋንጫ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው አመልክተዋል።

የዘንድሮው ውድድር ተሳታፊዎች ብዛት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ434 አትሌቶች ጭማሪ ማሳየቱን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም