ኢትዮጵያ ከማላዊ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከማላዊ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ታደርጋለች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማላዊ አቻው ጋር ዛሬ ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታውን ያከናውናል።
ጨዋታው ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል።
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ለወዳጅነት ጨዋታዎቹ ዝግጅት ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም ለ23 ተጫዋቾች ያደረጉ ሲሆን፣ ብሔራዊ ቡድኑ ከግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ሲያደርግ ቆይቷል።
ዋልያዎቹ ዛሬ ከሚያደርጉት የመጀመሪያ ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን ትናንት በድሬዳዋ ስታዲየም አከናውኗል።
ሁሉም የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የ55 ዓመቱ ዚምባቡዌያዊ አሰልጣኝ ካሊስቶ ፓሱዋ ለጨዋታው ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገው ቡድኑ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ነበልባሎቹ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ትናንት በድሬዳዋ ስታዲየም አድርጓል።
ኢትዮጵያ እና ማላዊ ከዚህ ቀደም በውድድር እና በወዳጅነት ጨዋታዎች 14 ጊዜ ተገናኝተዋል።
ዋልያዎቹ አራት ጊዜ ድል ሲቀናቸው ማላዊ አምስት ጊዜ አሸንፋለች። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ኢትዮጵያ በጨዋታዎቹ ላይ 16 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ ማላዊ 14 ጎሎችን አስቆጥራለች::
ሁለቱ ሀገራት ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2022 እና በ2023 በኮትዲቯር ለተካሄደው 34ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ባደረጉት የማጣሪያ ጨዋታ ነበር።
ከሁለቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል ማላዊ አንዱን ስታሸንፍ በቀሪው ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ኢትዮጵያ ማላዊን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈችው እ.አ.አ በ2021 በባህር ዳር ስታዲየም በተካሄደ የወዳጅነት ጨዋታ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ በወቅቱ የ4 ለ 0 ድል አስመዝግቧል።
እ.አ.አ 1983 ቡድኖቹ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ማላዊ ኢትዮጵያን 4 ለ 0 አሸንፋለች።
ጨዋታው፣ እ.አ.አ በ1986 በሜክሲኮ ለተስተናገደው 13ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የተደረገ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ነበር።
ሁለቱ ሀገራት ዛሬ ለ15ኛ ጊዜ ይገናኛሉ።
በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ 144ኛ፣ ማላዊ ደግሞ 127ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ብሔራዊ ቡድኖቹ ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታቸውን ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም በድሬዳዋ ስታዲየም ያደርጋሉ።
ዋልያዎቹ ጨዋታዎቻቸውን የሚያደርጉት፣ የፊፋ ዓለም አቀፍ የብሔራዊ ቡድኖች የጨዋታ ቀናትን (FIFA Window) በመጠቀም መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።