አዲስ የፎረንሲክና ስነ-ምረዛ ልህቀት ማዕከል የፍትህ ስርዓቱን በሳይንሳዊ ማስረጃ ለመደገፍና የህብረተሰብ ጤናን ለማላቅ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የፎረንሲክና ስነ-ምረዛ ልህቀት ማዕከል የፍትህ ስርዓቱን በሳይንሳዊ ማስረጃ ለመደገፍና የህብረተሰብ ጤናን ለማላቅ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ የፎረንሲክና ስነ-ምረዛ ልህቀት ማዕከል የፍትህ ስርዓቱን በሳይንሳዊ ማስረጃ ለመደገፍና የህብረተሰብ ጤናን ለማላቅ እንዲሁም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።
በዳግማዊ ምኒሊክ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተገነባው የዘረ-መል (DNA)፣ የፎረንሲክ እና ስነ-ምረዛ ምርመራ የልህቀት ማዕከል ዛሬ ተመርቋል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከድር እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አዲስ የተመረቀው የልህቀት ማዕከል በሀገሪቱ የፍትህ እና የሕክምና ዘርፍ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ ተጠቁሟል።
ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበት ወደ ውጭ ሀገር ተልኮ ይሰራ የነበረውን የዘረ-መል ምርመራ በሀገር ውስጥ መስጠት የሚያስችል ሲሆን የማንነት ማረጋገጥና የቤተሰብ ዝምድናን የመለየት ሥራን በሳይንሳዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ፣ ፍትህን ጥራት ባለው ማስረጃ በላቀ ሁኔታ ለመተግበር እንደሚረዳም ተጠቁሟል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ መንግሥት መከላከልንና አክሞ ማዳንን ያቀናጀ የጤና ፖሊሲ በመከተል ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ የተመረቀው የፎረንሲክ፣ የዘረ-መል እና የስነ-ምረዛ የልህቀት ማዕከል ለኅብረተሰቡና ለፍትሕ ሥርዓቱ በአንድ መስኮት የተቀላጠፈ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
ማዕከሉ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ፣ ለሀገሪቱ አክሞ የማዳን ተግባርና በዘርፉ ባለሙያዎችን ለማሠልጠን ትልቅ ተደማሪ አቅም እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የፎረንሲክ ምርመራ የሚሰጡ አምስት ተቋማት እንደሚገኙና ስድስተኛው ደግሞ በቅርቡ አገልግሎት መጀመሩን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ በከተማዋ ዘመኑን የዋጁ ግዙፍ ሆስፒታሎችን የመገንባት፣ በዘመናዊ መሣሪያዎች የማደራጀትና የነባር ተቋማትን አቅም የማሳደግ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተደራሽነትንና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፣ የልህቀት ማዕከሉም የፍትሕ ሥርዓቱን በሳይንሳዊ ማስረጃ ለመደገፍና የሕዝብ ጤናን ለማላቅ እንደሚረዳ አስረድተዋል።
አክለውም ማዕከሉ መዲናዋን የሚመጥን የጤና አገልግሎት ለመስጠትና አዲስ አበባን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ብሔራዊ ራዕይ ለማሳካት የላቀ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።