ቀጥታ፡

ተለዋዋጩን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በሳይንሳዊ መንገድ በመተንተን ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)፦ አሁናዊውንና ተለዋዋጩን ዓለም አቀፋዊ እንዲሁም ቀጣናዊ ሁኔታዎችን በሳይንሳዊ መንገድ በመተንተን ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰው ኃይሉን ለማብቃትና ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ በጀመረው አጠቃላይ የሪፎርም ሥራ መሠረት፣ ባለፉት ቀናት በነባራዊ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ሲከታተሉ ለቆዩ አመራሮችና ሠራተኞች የሥልጠና ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር አካሂዷል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀያየሩ በመሆናቸው፣ ሂደቶቹን በሳይንሳዊ መንገድ መገምገም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተለዋዋጭ ሁኔታዎች በጥልቀት በመገንዘብ፣ ለፖሊሲ ውሳኔዎችና ስልታዊ እርምጃዎች የሚጠቅሙ ምክረ-ሐሳቦችን ለማቅረብ የዲፕሎማቶችን ሙያዊ ብቃት ማጎልበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የተዘጋጀው ሥልጠና ተሳታፊዎቹ ወቅታዊ የዓለም ክስተቶችን በሙያዊ ዕይታ ለመተንተንና ክህሎታቸውን ለማሳደግ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ ሥልጠናው የተቋሙን የሰው ኃይል ክህሎትና ብቃት ለመገንባት የታለመው የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ስትራቴጂክ ዕቅድ በተለያዩ እርከኖች ላይ የሚገኙ ሠራተኞች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በተሻለ ሁኔታ ለማስከበር የሚያስችላቸውን አቅም የሚፈጥር ነው።

ስልጠናውን የሰጡት የቪየና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር ማርከስ ኮርንፕሮብስት (ዶ/ር) የምንኖርበት ዓለም በየወቅቱ ተለዋዋጭ እና ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም ስለ ወቅታዊ ለውጦች፣ ስለ ዓለም አቀፉ ሥርዓት፣ ስለ መላው አፍሪካ እንዲሁም ስለ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ጠቃሚ ውይይቶች የተደረጉበት የሥልጠና ጊዜ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም