ምርጫው የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በጉልህ የታየበት ነው - ፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በጉልህ የታየበት ነው - ፌዴሬሽኑ
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 28/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በጉልህ የታየበት መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አለሚቱ ሀይለሚካኤል በዚህ ወቅት እንደገለጹት ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ተአማኒ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ፌደሬሽኑ የድርሻውን ተወጥቷል፡፡
በምርጫው ሂደት ሴቶች ከመራጭነት ባለፈ በቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ታዛቢነት በመሳተፍ ለምርጫው ስኬታማነት ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደተካሄደ ማረጋገጣቸውን ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል፡፡
የፌደሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ወይዘሮ ማስረሻ ዘሪሁን በበኩላቸው በዘንድሮ ምርጫ ሴቶች የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ ይህም ሴቶች ዴሞክራሲን በማጽናት ሀገርን ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ሴቶች በምርጫው ሂደት እንዲሁም በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያደረጉት ንቁ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ በሆነ መንገድ መካሄዱን ያነሱት ደግሞ የፌደሬሽኑ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማስረሻ ከበደ ናቸው።
በምርጫው አጠቃላይ ሂደት የፌዴሬሽኑ አባል አደረጃጀቶች በንቃት ተሳትፈዋል ብለዋል።
ሴቶች በታዛቢነት ያደረጉት ከፍተኛ ተሳትፎ ለምርጫው ተአማኒነት እና አካታችነት የራሱን ሚና መጫወቱንም አመልክተዋል።
የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እያደገና የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።