የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአምስት ወራት ለ70 የመገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አገልግሎቶችን ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአምስት ወራት ለ70 የመገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አገልግሎቶችን ሰጠ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባለፉት አምስት ወራት ለ70 የመገናኛ ብዙኃን በፍቃድና ክትትል ዘርፍ የፍቃድ እና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንዲሁም የዕድሳት አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት የሚዲያ ዘርፉን እድገት የሚመጥን ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ሁለን አቀፍ የሪፎርም ስራዎች እያካሄደ እንደሚገኝ አመልክቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የሀገሪቷን መገናኛ ብዙኃን በቁጥር፣ በዓይነት እንዲሁም በተደራሽነት እድገት እንዲያስመዝግቡም የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ እንደሆነም ገልጿል።
በዚህም መሰረት ባለፉት አምስት ወራት (ከጥር እስከ ግንቦት ወራት 2018 ዓ.ም) በባለሥልጣኑ የሀገር ውስጥ ፈቃድ ምዝገባና ብቃት ማረጋገጫ የተሰጣቸውና ዕድሳት የተደረገላቸው የንግድ መገናኛ ብዙኃን፣ የማህበረሰብ እና የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የሚዲያ ፕሮግራም ዝግጅትን ጨምሮ 33 ተቋማት ናቸው።
የውጭ ሚዲያን በተመለከተ ደግሞ 16 ቋሚ የዜና ወኪሎች እና 21 በአጭር ጊዜ ዘገባ ፈቃድ የወሰዱ እና የዘጋቢ ፊልም ቀረፃ ፈቃድ የወሰዱ የውጭ ድርጅቶች እንደሚገኙበት ኢዜአ ከባለስልጣኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።