ቀጥታ፡

ለጤናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በመዲናዋ አዳዲስ ሆስፒታሎችን የመገንባትና ነባሮችን የማደስ ሥራዎች ተከናውነዋል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)፦ ባለፉት አምስት ዓመታት ለጤናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በአዲስ አበባ አዳዲስ ሆስፒታሎችን የመገንባትና ነባሮችን የማደስ ሥራዎች መከናወናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ፣ የሕዝባችንን የጤና አገልግሎት በአዲስ ከፍታ ላይ የሚያስቀምጥ አዲስ የዲኤንኤ(DNA)፣ የፎረንሲክና ስነምረዛ ምርመራ የልህቀት ማዕከል ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አመልክተዋል።

የልህቀት ማዕከሉ ኢትዮጵያ ብዙ የውጭ ምንዛሪ የምታጣበት እና የምርመራ ውጤት ለማግኘት በጣም ረጅም ጊዜ ይፈጅ የነበረውን ችግር የሚያስቀር ነው ብለዋል።

የልህቀት ማዕከሉ በዘር መለያ (DNA) መረጃ ማከማቻና ማነጻጸሪያ ሲስተም (CODIS)፣ በወንጀል የተጠረጠሩ፣ ወላጅነትን ለማረጋገጥና መሰል ምርመራዎችን በዘር መለያ (DNA Profiling) ለመለየት፣ የቤተሰብ ግንኙነትን እስከ ዘር ሀረግ መለየትና ማረጋገጥ እንዲሁም አጠራጣሪ ማንነትን ለማወቅ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ማዕከል የሀገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት ምርመራን ውጤታማ በማድረግና በማዘመን፣ በሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የወንጀል ምርመራ ለማካሄድ፣ የመብት ጥያቄዎችን ለመመለስና ለሕዝብ ጤና ጥበቃ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ብሔራዊ የልህቀት ማዕከል እንደሆነም ነው ያብራሩት።

ሁሌም ቃልን በተግባር ፈፅመን በቁርጠኝነትና በተሻሻለ የስራ ባህል በመስራት ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት አራት ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመጥኑ ሆስፒታሎች በመገንባትና ነባሮቹን ሆስፒታሎች በማደስና በማስፋፋት ሰፊ ስራዎችን በማከናወን መዘመናቸውን አስረድተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በጤናው ዘርፍ የሀገርን የዕድገት ተምሳሌትነት እና የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ምዕራፍ እያበሰርን ነው፤ ይህም ተጠናክሯል ብለዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የጤና ባለሙያዎች ትጋትና ብቃት ይበልጥ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

ከንቲባዋ ከዕቅድ ዝግጅት ጀምሮ የልህቀት ማዕከሉ እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ በራሳቸው፣ በከተማ አስተዳደሩ እና በተጠቃሚው ሕዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም