ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዲጂታላይዜሽን የሚመራ ኢኮኖሚ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት ይሰራል

ጎንደር፤ ግንቦት 28/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዲጂታላይዜሽን የሚመራ ኢኮኖሚ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በኢኖቬሽን ዘርፍ የተቀረፁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በአግባቡ መተግበር የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ለማበረታታት ያቋቋመው የቢዝነስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ማእከል በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ ጀምሯል።


 

ዩኒቨርሲቲው የማእከሉን ተልአኮና አላማ ማሳካት እንዲቻል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የስምምነት ፊርማም ዛሬ አከናውኗል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዲጂታላይዜሽን የሚመራ ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል።

ኢኖቬሽንን ከማበረታታትና ከመደገፍ አንጻር ለፈጠራ ሃሳቦችና ስታርታፖች ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ከምርምርና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቁርኝት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ የማህበረሰቡን ችግር በመፍታት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎና አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከዚህ አንጻር ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፋጠን ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ በማተኮር እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር ተግባራት ሞዴል መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ለማበረታታት ያቋቋመው የቢዝነስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ማእከል የፈጠራ ሃሳቦች በልጽገው ወደ ተግባር የሚሸጋገሩበትን ምቹ የቴክኖሎጂ አውድ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡


 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው ማእከሉ የምርምር ሃሳብ ያላቸውን ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን በመቀበል ሃሳባቸውን ወደ መሬት የሚያወርዱበትን ምቹ የቴክኖሎጂ አውድ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሰቲው ማእከሉን በቴክኖሎጂ፣ በባለሙያዎችና በዘመናዊ መሳሪያዎች በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገባ ማድረጉን ጠቁመው ስራ ፈጣሪዎች ምርምርና የፈጠራ ሃሳባቸው አድጎ ወደ ገበያ እንዲወጣ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ማእከሉ ችግር ፈቺ የምርምር ሃሳቦች ከመደርደሪያ ወርደው ወደ ኢንዱስትሪዎችና ካምፓኒዎች እንዲሸጋገሩ ብሎም የማህበረሰቡን ችግር መፍታት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር በመግለጽ።

በማእከሉ የምረቃ ስነ ስርአት ላይ የአፍሪካ ልህቀት ማእከል ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብረሃን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም