የሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው ሀገራት የኃይል አቅርቦትን ከማረጋገጥ ባለፈ በትብብር ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ለማጠናከር ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው ሀገራት የኃይል አቅርቦትን ከማረጋገጥ ባለፈ በትብብር ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ለማጠናከር ያግዛል
አሶሳ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው ሀገራት የኃይል አቅርቦትን ከማረጋገጥ ባለፈ በትብብር ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተመላከተ።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣናዊ ትብብርን በማሳለጥ እና የአባይ ተፋሰስን በዘላቂነት ማልማት ላይ ያተኮረ 4ኛው አለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ አካሂዷል።
በወቅቱም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንደገለፁት፤ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናው ሀገራት የኃይል አቅርቦትን ከማረጋገጥ ባለፈ በትብብር ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ለማጠናከር ያግዛል።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ የምርምር ስራዎችን በማጠናከር ሀሰተኛ ክሶችንና መረጃዎችን መመከትና እውነቱን ማስረዳት ከምሁራን ይጠበቃል ብለዋል።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ለግድቡ ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ መሰል የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማጠናከር የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለቀጣናው ሀገራት የሚያስገኘውን ፋይዳ ማሳወቅ እንደሚገባው አመልክተዋል።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ያሬድ ሙሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በግድቡ አካባቢው የሚኖረው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ የአፍሪካና የአውሮፓ ሀገራት የዘርፉ ተመራማሪዎች በበይነ መረብ ጥናታቸውን ያቀረቡ ሲሆን በግድቡ እና በአባይ ተፋሰስ ልማት ዙሪያ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።