በጤናው ዘርፍ የኢትዮጵያ የዕድገት ተምሳሌትነት በተግባር እየተረጋገጠ ይገኛል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በጤናው ዘርፍ የኢትዮጵያ የዕድገት ተምሳሌትነት በተግባር እየተረጋገጠ ይገኛል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2018(ኢዜአ)፦ በጤናው ዘርፍ የኢትዮጵያ የዕድገት ተምሳሌትነትና የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ምዕራፍ በተግባር እየተረጋገጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
በዳግማዊ ምኒሊክ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተገነባው የዘረ-መል (DNA)፣ የፎረንሲክ እና ስነ-ምረዛ ምርመራ የልህቀት ማዕከል በዛሬው ዕለት ተመርቋል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከድር እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አዲስ የተመረቀው የልህቀት ማዕከል በሀገሪቱ የፍትህ እና የሕክምና ዘርፍ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበት ወደ ውጭ ሀገር ተልኮ ይሰራ የነበረውን የዘረ-መል ምርመራ አገልግሎት በሀገር ውስጥ መስጠት ያስችላል ተብሏል።
እንዲሁም የማንነት ማረጋገጥና የቤተሰብ ዝምድናን የመለየት ሥራን በሳይንሳዊና ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ፣ ፍትህን ጥራት ባለው ማስረጃ በላቀ ሁኔታ ለመተግበር እንደሚረዳም ተጠቁሟል፡፡
ይህም የወንጀል ምርመራዎችንና ተያያዥ የሕክምና ፍተሻዎችን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ተጠቅሷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃው ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማዋ ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
በከተማዋ አራት አዳዲስ ሆስፒታሎች የተገነቡ ሲሆን፣ ሁለቱ ቀድመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰው ቀሪ ሁለቱ ደግሞ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ነው ያሉት፡፡
ከአዳዲስ ግንባታዎች በተጨማሪ የነባር ተቋማትን አቅም የማሳደግ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከለውጡ በኋላ የዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል በተሰሩ ዘላቂ ሥራዎች ስሙን ብቻ ይዞ የቆየውን ሆስፒታል የቀድሞ ስምና አንጋፋነቱን እንዲመልስ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ከተመረቀው ማዕከል በተጨማሪ፣ የሆስፒታሉ የዓይንና የኩላሊት ሕክምና አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን መደረጉን ማሳያ አድርገው ጠቅሰዋል።
በመዲናዋ በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አዲስ አበባን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዘርፉ አዲስ ብልፅግናን በማብሰር ሂደት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፤ ወደፊትም የሕክምና ተቋማትን ከመገንባትና በዘመናዊ መሣሪያዎች ከማደራጀት ባለፈ፣ ብቁ ባለሙያዎችን የማፍራት ሥራ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ መንግስት መከላከልንና አክሞ ማዳንን ያቀናጀ ፖሊሲ በመከተል ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ የተመረቀው የፎረንሲክ፣ የዘረ-መል እና የስነ-ምረዛ የልህቀት ማዕከል ለህብረተሰቡና ለፍትህ ስርዓቱ በአንድ መስኮት የተደራጀና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ማዕከሉ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ፣ ሀገሪቱ ለጀመረችው አክሞ የማዳን ተግባር ትልቅ ተደማሪ አቅም እንደሚሆንም ተናግረዋል።