በክልሉ የግብርና ቴክኖሎጂን በስፋት በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብርና ቴክኖሎጂን በስፋት በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል
መቱ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል የእርሻ መሬትን ከማስፋፋት ባለፈ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማጎልበት ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።
በኢሉአባቦር ዞን የመኸር አዝመራ በተጠናከረ መልኩ የቀጠለ ሲሆን በዛሬው ዕለት በዶረኒ ወረዳ የተዘጋጀ መሬት በበቆሎ ዘር የመሸፈን ስራ ተጀምሯል።
በዚሁ ጊዜ የኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ፤ በክልሉ የበጋና ክረምት እርሻ ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም በክልሉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመስኖ ልማት ስራ ትልቅ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው የአነስተኛ እና መለስተኛ መስኖ ልማት ግድቦች ግንባታ መጠናከሩንም ገልጸዋል።
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚቻለው በዋናነት ግብርናን በማስፋፋት መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር ግርማ፣ በበጋ ስንዴ ልማት በክልሉ ትልቅ ስኬት መመዝገቡን አስታውሰዋል።
ይህም ቀድሞ የነበረውን በዓመት አንዴ የማምረት ባህል በማሻሻል፣ ለክረምት እርሻው ተጨማሪ ትልቅ አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተያዘው የመኸር አዝመራም ለግብርና ልማት መዋል የሚችለውን መሬት አሟጦ በማረስ እና የግብርና ሜካናይዜሽንን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
በኢሉአባቦር ዞን በክረምት እርሻ 389 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።
በዞኑ ወረዳዎች የኩታ ገጠም እርሻዎችን በዘር የመሸፈን ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል።
በሁሉም ወረዳዎች ምርታማነትን የሚያሳድግ የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦት እያደገ መምጣቱን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ የክረምት እርሻው በትራክተር በመታገዝ እንዲታረስ ትኩረት መሰጠቱን አክለዋል።
የዶረኒ ወረዳ ግብርና ልማትና መሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ለሊሴ አመና በበኩላቸው፣ በወረዳው በክረምት እርሻ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም በተለይ የበቆሎ ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል።
በክረምት እርሻው ላይ የተሰማሩ የወረዳው አርሶ አደሮችም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚረዱ ሰብሎች ጎን ለጎን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን ሰብሎችም በትኩረት እንደሚያመርቱ ተናግረዋል።