ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረትና ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)አፍሪካ ህብረትና ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በአፍሪካ ህብረት የቻይና ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ጂያንግ ፌንግን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሊቀመንበሩና አምባሳደሩ በውይይታቸው በአፍሪካ ህብረት እና በቻይና መካከል ባለው ስትራቴጂካዊ ትብብር እንዲሁም የጋራ ፍላጎት በሆኑ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።


 

በውይይቱ ወቅት በቻይና-አፍሪካ ትብብር መድረክ (FOCAC) ስር የሚከናወኑ ተግባራትን ጨምሮ በአህጉሪቱና በቻይና መካከል ያለው ዘላቂ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
በተጨማሪም ቻይና አፍሪካ ቅድሚያ ለምትሰጣቸው የልማት ጉዳዮች የምታደርገውን ድጋፍ እና አዳዲስ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችም ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።

ቻይና ከአፍሪካ ጎን በመቆም ለምታሳየው ቀጣይነት ያለው አብሮነት ሊቀመንበሩ አድናቆታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በተለይም የኢቦላ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በተደረገው ዘመቻ ወቅት ላደረገችው ፈጣንና ወቅታዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሁለቱ ወገኖች በኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያም የመከሩ ሲሆን፤ ቻይና ከአፍሪካ ወደ አገሯ ለሚላኩ ምርቶች የዘረጋችውን የቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (ኢኒሼቲቭ) ዋንኛ ትኩረት ነው።

የአህጉሪቱን የረጅም ጊዜ የልማት ፍኖተ-ካርታ የሆነውን የአጀንዳው 2063 ግቦችን ለማሳካት፤ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረቱ አጋርነቶችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ሁለቱ ወገኖች ለሉዓላዊነት፣ ለግዛት አንድነት እና ለባለብዙ ወገን ትብብር መርሆዎች ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

የአህጉሪቱን ሰላም፣ ልማትና የጋራ ብልጽግና ለማረጋገጥም ይበልጥ ጠንካራ የአፍሪካ ህብረትቻይና አጋርነት መፍጠር እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም