ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ለተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ስኬት የጎላ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ለተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ስኬት የጎላ ሚና አላቸው
ጎንደር፤ ግንቦት 28/2018(ኢዜአ)፦ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ለተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ስኬት የጎላ ሚና እንዳላቸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ "በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በጤና፣ በኑሮና በስነ ምህዳር ላይ ዘላቂ አቅምን መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ 32ኛውን ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ እያካሄደ ነው።
ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በጉባኤው እንደገለጹት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተገኘው ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ለዲጂታል 2030 ግብ ስኬት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የላቀ አበርክቶ ሊኖራቸው ይገባል።
በኢትዮጵያ እየተሰጠ ያለው የ5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወጣቱ ትውልድ የመጪው ዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀት ባለቤት እንዲሆን አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።
የዲጂታል መሠረተ ልማት ተደራሽነትን ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት ለዲጂታል ኢኮኖሚው መጠናከር መሠረት መጣሉንም ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው በፈጣንና ተለዋዋጭ አለም ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂን አስፈላጊነት በመረዳት ዩኒቨርሲቲው ምርምር ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በዚህም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምርምርና የፈጠራ ስራዎችን በማበረታታት በዘርፉ ብቁ ተመራማሪዎችን ለማፍራት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው ይህም ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በይፋ ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ የዘመኑ ትውልድ የወደፊቱን አለም መቀላቀል እንዲችል የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ባለቤት መሆን አለበት ብለዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አብዮት ኢትዮጵያ ተቀላቅላ መጓዝ ትችል ዘንድ ምሁራን በጥናትና ምርምር ማገዝ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች በሚቀርቡ የምርምር ስራዎች ላይ እየተወያዩ ነው።
በጉባኤው ላይ የተዘጋጀው የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ኤግዚቢሽንም በዛሬው ዕለት ለእይታ ክፍት ተደርጓል።