ቀጥታ፡

ህዝቡ በምርጫው ያሳየውን ተሳትፎ በሀገር ግንባታና በልማት መድገም አለበት - አባገዳዎችና ኡጋዞች

ድሬደዋ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦ ህዝቡ በምርጫው ሂደት ያሳየውን ጠንካራ ህዝባዊ ተሳትፎ በሀገረ መንግሥት ግንባታና በዘላቂ ልማት ስራዎች ሊደግመው እንደሚገባ በድሬዳዋ የሚገኙ አባገዳዎችና ኡጋዞች አስገነዘቡ።

በድሬዳዋ አስተዳደርና በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል። 

ይህ በምርጫ ወቅት የታየው ከፍተኛ የሕዝብ መነሳሳትና አንድነት ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው በአስተዳደሩ አባገዳዎችና ኡጋዞች ያሳሰቡት።

በድሬደዋ የሚገኙ የአፍረንቀሎ፣ የኢሳ እና የጉርጉራ ማህበረሰብ ባህላዊ መሪዎች  ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክተው ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች የሚፈልጉትን በነፃነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመምረጥ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የድርሻቸውን ተወጥተዋል።

የኦሮሞ አፍረንቀሎ አባገዳ አብዱረዛቅ አህመድ፤ ድሬዳዋን ጨምሮ በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኘው ማህበረሰብ በጠቅላላ ምርጫው በነቂስ ወጥቶ በመሳተፍ ለሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርአት መዳበር የድርሻውን ተወጥቷል ብለዋል።

ማህበረሰቡ በምርጫው ላይ ያሳየውን ተሳትፎ በሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ዘላቂ ሰላም በማጽናትና ልማትን ዕውን በማድረግ ረገድ ማስቀጠል አለበት ብለዋል።

የሶማሌ የኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊ መሪ ኡጋዝ ተወካይ ሼህ አብዶ ኡመር በበኩላቸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈልገውን ፓርቲ በነፃነት መምረጡን አንስተዋል።

ህብረተሰቡ በምርጫው ያሳየውን ጠንካራ ተሳትፎ በማስቀጠል ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር አንድነቱን ጠብቆ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ ዕድገት እና ከፍታ ለማስቀጠል እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ እና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነቱን ባረጋገጠ መንገድ መካሄዱን የተናገሩት ደግሞ የጉርጉራ ማህበረሰብ ባህላዊ ማዕከል አፈጉባኤ ሱልጣን  አብዲ ኡስማን ናቸው።

ሱልጣን አብዲ አክለው እንዳሉት፤ ዜጎች በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን መብት በምርጫው በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግስትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መዳበር የድርሻቸውን ተወጥተዋል።

ይህንን ጠንካራ ተሳትፎ  ዘላቂ ዕድገት እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም