በፓርኩ ለአቮካዶ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርት የሚያቀርቡ ማህበራት ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በፓርኩ ለአቮካዶ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርት የሚያቀርቡ ማህበራት ተጠቃሚ ሆነዋል
ሀዋሳ ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ማቀነባበሪያ ፓርክ ከአምራች ኢንዲስትሪዎች ጋር በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ተጠቃሚ መሆናቸውን በአቮካዶ ምርት ማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ የአርሶ አደር ማህበራት ገለጹ።
በይርጋለም ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚንቀሳቀሱ 10 አምራች ኢንዱስትሪዎች አራቱ በአቮካዶ ዘይት ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ይህም ለአካባቢው አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ እያደረጋቸው ነው።
በተለይም አርሶ አደሩ በሕብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅቶ ምርቱን ለኢንዱስትሪዎች እንዲያቀርብ ምቹ ዕድል እየፈጠረ መጥቷል፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ማህበራት መካከል የ"ዶንጎራ ቀዋዶ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና አቅራቢ ማህበር" ሰብሳቢ አቶ ላታሞ ያዕቆብ እንደገለጹት፤ ማህበሩ በአምስት መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማህበራት በርካታ አርሶ አደሮችን አቅፎ የአቮካዶ ምርትን ለኢንዱስትሪዎች እያቀረበ ይገኛል።
ይህም ቀደም ሲል አርሶ አደሩ ገበያን በማፈላለግ ያጋጥመው የነበረውን የምርት፣ የጊዜና የጉልበት ብክነት በማስቀረት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።
የማህበሩ አባላት የአቮካዶ ምርታቸውን በማህበሩ በኩል በቀጥታ ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ገቢያቸውን እያሳደጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሌላው የ”ፋያ ኢንተርፕራይዝ ማህበር” ሰብሳቢ ወጣት ሻላ ካሳ፤ በማህበር ተደራጅተው የአቮካዶ ምርትን በፓርኩ ውስጥ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ገልጿል።
በቀን ከ50 ሺህ እስከ 80 ሺህ ኪሎ ግራም የአቮካዶ ምርት ሰብስበው እንደሚያቀርቡ ገልጾ፣ በምርት አሰባሰብ ሂደት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብሏል።
አሁን ላይ ገቢና ተጠቃሚነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም ተናግሯል።
የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀይሉ የተራ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በፓርኩ በአቮካዶ ዘይት ለተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተደራጅተው ምርት የሚያቀርቡ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።
ፓርኩ ወደሥራ ከገባ ያለፉት አምስት ዓመታት ከ83ሺህ ቶን በላይ የአቮካዶ ምርት ለፓርኩ መቅረቡን የጠቆሙት አቶ ሀይሉ፣ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል።
በማህበር ተደራጅተው ለኢንዱስትሪዎቹ የአቮካዶ ምርት የሚያቀርቡ አርሶ አደሮችም ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል።
አቶ ሀይሉ እንዳሉት በ43 ማህበራት የተደራጁ ከ132ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለፓርኩ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡