ቀጥታ፡

ስልጠናው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጎልበት ያስችላል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)፦በኢንስቲትዩቱ የተዘጋጀው ሥልጠና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገርና ዘላቂ ወዳጅነትን ይበልጥ ማጎልበት የሚያስችል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ቀጣናዊ ትብብር፣ የአቅም ግንባታ እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥልጠና ለደቡብ ሱዳን ዲፕሎማቶች መስጠት ጀምሯል።


 

ስልጠናው በድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች አጠቃቀም፣በፓን አፍሪካኒዝም እንዲሁም በዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳንን ጥልቅ ታሪካዊ፣ የባህል፣ የቋንቋና የድንበር ተሻጋሪ ማንነት ትሥሥር አውስተዋል።

ሁለቱ አገራት የተጠናከረ ወዳጅነትና ጉርብትና ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ጠንካራ የጋራ መጻኢ ዕድልን ለመቅረጽ ወሳኝ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የተዘጋጀው ሥልጠናም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና ዘላቂ ወዳጅነትን ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

ሥልጠናው በቀጣናዊ ትብብርና በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ የዲፕሎማቶች ሚና ምን መሆን እንዳለበት ሰፊና ጠቃሚ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን አክለዋል።

ዲፕሎማቶች በጋራ ሀብቶች አጠቃቀም፣በፓን አፍሪካኒዝም፣ በዓለም አቀፍና ቀጠናዊ ጉዳዮች ያላቸው ሚና የጎላ በመሆኑ ለጋራ ጉዳዮች በጋራ መቆም እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ቶክ ዴንግ፣ ስልጠናው የአቅም ግንባታንና ንቁ የልምድ ልውውጥን ከመፍጠር ባለፈ፣በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን የትብብርና ጥልቅ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም