ቀጥታ፡

የሀገርን ዕድገት ለማረጋገጥና የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት በትብብር መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን

ድሬዳዋ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦ የሀገርን ዕድገት ለማረጋገጥና የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት በትብብር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በድሬዳዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

በድሬደዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤቱ ሰብሳቢ እና የኢዜማ የድሬዳዋ እና የሐረሪ ክልል  አስተባባሪ አቶ ዮናስ በትሩ፤ ጠቅላላ ምርጫውን አስመልክተው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ጠቅላላ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተካሂዶ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ህዝቡ ለሀገሩ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መጎልበት ያለውን ጠንካራ ፍላጎት በየምርጫ ጣቢያዎቹ በማለዳ በመገኘት ድምፅ ሲሰጥ ማስተዋላቸውን አንስተዋል።

መራጩ ህዝብ በማለዳ በመሰለፍ የሚፈልገውን ፓርቲ በነፃነት መምረጡን አስታውሰው የህዝብን ድምፅ ማክበርና ውጤቱን በፀጋ ለመቀበል ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በህዝብ ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት ለማግኘት የሚያስችሉ ስራዎችን በትብብር  ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ ዮናስ ገለፃ፤ ምክር ቤቱ በሀገረ መንግስት ግንባታ እና የህዝብን ኑሮ ለመወለጥ በሚከናውኑ ሀገራዊ ተግባራት ላይ የድርሻውን ለመወጣት ተዘጋጅቷል።

የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች የመጠበቅና የማስከበር እንዲሁም ጠንካራ ሀገረ መንግስትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባት ጉዳይ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በመግለፅ።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በድሬዳዋ ገጠርና ከተማ በሚገኙ 297 የምርጫ ጣቢያዎች መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም