በኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት 16 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ተመርቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት 16 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ተመርቷል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦ በኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው የምርት ዘመን 16 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል አጠቃላይ የቡና ምርት መገኘቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የቡና ጥራት እና ልማት ዳይሬክተር አቶ ታከለ ኃይለማርያም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የቡና ልማት በልዩ ኢንሼቲቭ ተቀርጾ ወደ ስራ ከገባ ወዲህ፣ የቡና ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል።
የአርሶ አደሩ ህይወትና ኑሮ ከቡና ልማት ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ የቡና ልማቱ በስፋትና በዘመናዊ መልኩ መከናወኑ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።
ቢሮው የቡና ምርትን በዓይነትና በብዛት ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን ተግባራዊ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ከእነዚህም መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ለአርሶ አደሩ ማድረስ፣ ያረጁና ምርት የማይሰጡ የቡና ተክሎችን በአዲስ የመተካት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ የቡና ተክሎችን የመጎንደል ስራን በስፋት ማከናወን መቻሉንም ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ በ2018 የምርት ዘመን 18 ሚሊዮን ኩንታል የቡና ምርትን ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ በእስካሁኑ ሂደት 16 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል።
ቡና በዓለም ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነትና ጥራት ለማስጠበቅ አርሶ አደሩን ማዕከል ያደረጉ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ ታከለ አብራርተዋል።
በተለይም አርሶ አደሮች የደረሰ ቀይ ቡና ብቻ እንዲለቅሙ ማድረግ የተቻለ መሆኑን የገለጹ ሲሆን የተሰበሰበውን ቡና በጥራት የማድረቅ ባህል ማደጉን ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩን የምርት ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግና ህገ-ወጥ ደላሎችን ለመከላከል፣ ምርቱን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል።