ቀጥታ፡

በዞኑ በሚገኙ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የነዋሪውን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው

ደሴ ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦በደቡብ ወሎ ዞን በሰባት ከተማ አስተዳደሮች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የነዋሪውን የልማት ተጠቃሚነት እያሳደገ መምጣቱን የዞኑ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የመሰረተ ልማት ቡድን የኮንስትራክሽን አስተዳደር መሃንዲስ አደም መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ የሕብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።

በተለይ ከተሞችን በኮሪደር ልማት በማስዋብና በማሳመር ለነዋሪዎች፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

በዚህም በሐይቅ፣ ሀርቡ፣ ጊምባ፣ ወረኢሉ፣ መካነሰላም፣ አቀስታ እና ደጎሎ ከተማ አስተዳደሮች የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

እስካሁን በተደረገ የተቀናጀ ጥረት በተወሰኑ ከተሞች የኮሪደር ልማቱን አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል።

ቀሪውንም የልማት ስራ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ መዝናኛና ሌሎችንም ያካተተ በመሆኑ ከተሞችን በማነቃቃት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳስቻለም አብራርተዋል።

ለኮሪደር ልማት ስራው ከ527 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለት እየተከናወነ ሲሆን ህብረተሰቡ ገንዘብ በማዋጣት፣ በጉልበቱና የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የሐይቅ ከተማ ነዋሪ አቶ እንድሪስ ሰይድ በሰጡት አስተያየት፣ የከተማው የኮሪደር ልማት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ለነዋሪዎች ምቹ ከመሆኑ ባለፈ ከተማው እንዲነቃቃ አድርጓል።

በፍጥነት የተጠናቀቀው ኮሪደሩ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ ሌሎችንም መዝናኛዎች ያካተተ በመሆኑ የተሽከርካሪ አደጋንም መቀነስ አስችሏል ብለዋል።

የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እናትነሽ በሽር በበኩላቸው፣ ''የከተማው የኮሪደር ልማት በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት እንዲጀምር እኛም በገንዘብ፣ በጉልበትና በሀሳብ የድርሻችንን ተወጥተናል'' ብለዋል።

ልማቱ የከተማውን ውበት ከማሳመር ባለፈ ከተማው የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆንም እያገዘ እንደሆነ አንስተዋል።

''ከተማችን በኮሪደር ልማት እየተዋበችና እየደመቀች በመሆኑ ተደስተናል'' ያሉት ደግሞ የሀርቡ ከተማ ነዋሪ አቶ አሊ አህመድ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም