ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ እና የምርጫ ቦርድ የማስፈፀም አቅም እያደገ መምጣቱ የታየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ እና የምርጫ ቦርድ የማስፈፀም አቅም እያደገ መምጣቱ የታየበት ነው
አዲስ አበባ፤ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)፦ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማስፈፀም አቅም እያደገ መምጣቱ የታየበት ስኬታማ ምርጫ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ፡፡
ምክር ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት በኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግበው ዕውቅና ያገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በመወከል በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ፈቃድ አግኝቷል፡፡
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ሚና ተወጥቷል፡፡
በቅድመ ምርጫ ወቅት የምርጫ ትምህርትና ግንዛቤ በመፍጠር፣የፓርቲዎችን የክርክርና የግልጽነት መድረኮች ማመቻቸቱን አስታውሰዋል፡፡
ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ መታዘባቸውን በመጥቀስ፤ምርጫው በርካታ ዜጎች የተሳተፉበት፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሂደትን የተከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት በትዕግስት መምረጡንና በንቃት መሳተፉን በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ባደረጉት የመታዘብ ሥራ ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
በምርጫው አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ወጣቶች፣ ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ድምጻቸውን እንደሰጡም ነው የገለጹት፡፡
ይኸውም የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና ይበልጥ አካታች ተሳትፎን እያጎለበተ መምጣቱን ማሳያ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፥ መንግሥት፣የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎችም አጋር አካላት ለምርጫው ስኬታማነት ሚናቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
የዲሞክራሲና የፍትሕ ተቋማት እንዲጠናከሩ በትኩረት መሰራቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ቦርዱ ነፃና ገለልተኛ በመሆን የማስፈጸም አቅሙ እያደገ መምጣቱን በማንሳት፤ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ምርጫ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መገለጫ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፥ ስልጡን የፖለቲካ ባህልንና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥትን ለመገንባት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያም የዲሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት የሁሉም አካላት ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።