በአራት ክልሎች የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአራት ክልሎች የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው
ደብረብርሃን ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦ በአራት ክልሎች የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ቅኝት ምላሽ ሰጪ ባለሙያ አቶ ታደሰ ያለው እንደገለጹት፤ ክትባትን በመጠቀም የበለፀገና ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
በዚህም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከዛሬ ግንቦት 28 እስከ ሰኔ 2/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
በሚሰጠው ክትባትም 418 ሺህ 569 ህፃናትን ለመድረስ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው ክትባቱም በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት፣ በቤት ለቤትና ህጻናት በሚገኙበት አካባቢ ይሰጣል ብለዋል።
ማህበረሰቡም በአካባቢያቸው የሚገኙ ህፃናትን በማስከተብ ከበሽታው ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዛሬ መሰጠት ከተጀመረባቸው አካባቢዎች መካከል የደብረ ብርሃን ከተማ አንዱ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ጤና ማምሪያ ኃላፊ አቶ በቀለ ገብሬ ፤ ክትባቱ በጤና ተቋማት፣ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች፣ በቤት ለቤት ዘመቻ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም ህፃናትን በማስከተብ ጤናማና አምራች ማህበረሰብ ለመገንባት የተያዘውን ግብ ለማሳካት የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።