ቀጥታ፡

በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ

ዱራሜ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና ዘርፍ ያሉ ፀጋዎችን ለልማት በማዋል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከተለያዩ ዞኖች እና ከጠምባሮ ልዩ ወረዳ ለተውጣጡ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ያዘጋጀው የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና በዱራሜ ከተማ እየተሰጠ ነው። 


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ፀጋዎችን ወደልማት በመቀየር ከዘርፉ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ።

ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የቴክኖሎጂ ሽግግር ወሳኝ እንደሆነ ያነሱት አቶ ኡስማን፣ ለዚህ ስኬትም የግብርና ልማት ጣቢያ ሠራተኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። 

የአካባቢውን ፀጋ ለይቶ በማልማት ረገድ በተሰራው ሥራ በርካታ አርሶ አደሮች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸው፣ በዚህም አርሶ አደሮች ከራሳቸው ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።

በተጨማሪም የኢንዱስትሪና የወጪ ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት።

በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ወጥነት ባለው መልኩ ለማጠናከር ለግብርና ልማት ጣቢያ ሠራተኞች የዛሬው የአቅም ግንባታ ስልጠና መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ሠራተኞቹ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸውም አቶ ኡስማን አሳስበዋል። 


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቡቶ አኒቶ በበኩላቸው እንዳሉት፤ አርሶ አደሩን በቅርበት በመደገፍ ምርትና ምርታማነቱ እንዲጨምር በማድረግ በኩል የግብርና ልማት ጣቢያ ሠራተኞች ሚና የጎላ ነው።

ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሩ በማሸጋገር፣ ግብርናን በማዘመንና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና ማጠናከር እንዳለባቸውም አፈ ጉባኤው አሳስበዋል። 

በመድረኩ ከከምባታ እና ከሀድያ ዞኖች እንዲሁም ከጠምባሮ ልዩ ወረዳ የተውጣጡ ከ1ሺህ 700 በላይ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች እና የተለያዩ የሥራ ሀላፊዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም