ቀጥታ፡

በምርጫው ያደረግነውን ጠንካራ ተሳትፎ ሰላምን በማጽናትና በልማት ለመድገም ተዘጋጅተናል- ወጣቶች

ገንዳ ውሃ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦ ለምርጫው ስኬት ያደረግነውን ጠንካራ ተሳትፎ በዘላቂ ሰላምና ልማት ስራዎች በመድገም በጋራ ሀገር ለማጽናት ተዘጋጅተናል ሲሉ በምእራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በስኬት መከናወኑ ይታወቃል።

የምርጫ ሂደቱና የድምፅ አሰጣጡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጸዋል። 

የምርጫ ካርድ ከመያዝ ጀምሮ እስከ ድምፅ አሰጣጡ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ህዝቡ በድምፁ ውሳኔ የሚሰጥበትና የስልጣን ባለቤት መሆኑን ያሳየበት ስኬታማ ምርጫ መሆኑም ተገልጿል። 

ኢዜአ በአማራ ክልል ምእራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ ያነጋገራቸው ወጣቶች፤ የምርጫው ሂደት ሀገር ለማጽናት ጠንካራ ተሳትፎ ያሳየንበት ታሪካዊ ክስተት ነበር ብለዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ገብረዮሃንስ ጓዴ እና አበበ ምስጋናው፤በህዝቡ በድምፅ አሰጣጡ የታየው ተሳትፎ ሀገር ወዳድነቱን ያሳየበት መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ለምርጫው ስኬት ያደረግነውን ጠንካራ ተሳትፎ በዘላቂ ሰላምና ልማት ላይም በመድገም ኢትዮጵያን በጋራ ለማጽናት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ወጣት ብሩክ ወርቄ፤ በምርጫው ያሳየነውን ጠንካራ ተሳትፎ በቀጣይ በሀገር ልማትና በሰላም ግንባታ ሂደት ማስቀጠል ይጠበቅብናል ለዚህም ተዘጋጅተናል ብሏል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም