ቀጥታ፡

በምርጫው ያሳየነውን ንቁ ተሳትፎ በልማት ለመድገም ተዘጋጅተናል

ሐረር ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦ በምርጫ ወቅት የታየውን ጠንካራ የሕዝብ ተሳትፎና አንድነት በልማት ሥራዎች ላይም በመድገም የሀገራቸውን ዕድገት ለማፋጠን ዝግጁ መሆናቸውን በሐረር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረር ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በምርጫው ላይ ያሳዩትን ተሳትፎ በቀጣይ የልማት ስራዎችን በማጠናከር ልማትና እድገትን ማስቀጠል ይጠበቅብናል  ብለዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሙሉነሽ ዋቅቶላ እንዳሉት፤ ምርጫው ህዝቡ በነቂስ በመውጣት ሀገር ወዳድነቱን በግልጽ ያሳየበት ነው።

በምርጫ ያሳየነውን ተሳትፎ  በማጎልበት እና የልማት ስራዎችን በማስቀጠል መድገም ይጠበቅብናል  ብለዋል።

መምህር ቶማስ ዱባለ ፤ምርጫው የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ትልቅ ስኬት ያሳየ ነው ሲሉ አክለዋል። 

ከዚህም ባለፈ የተጀመሩትን የልማት ስራዎች በማፋጠን  ለሀገር ልማት መትጋት ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ታደሰ በየነ በበኩላቸው፤ ምርጫው የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ የታየበት፣ የሀገሪቱን የወደፊት ብሩህ ተስፋ ያሳየና የሚያስደስት እንደነበር አስታውሰዋል።

በቀጣይም በምርጫው ላይ ያደረጉትን ተሳትፎ  በልማት ሥራዎች ላይ በመድገም ለልጅ ልጆቻቸው ብሩህ ሀገርን የማሻገር ተግባር እንደሚያከናውኑ ጠቅሰዋል።

ምርጫው በርካታ ዜጎች የተሳተፉበትና ሰላማዊ መሆኑ በእጅጉ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ መምህር ደረጀ ተስፋዬ ናቸው።

መምህር ደረጃ ፤ በቀጣይም ሀገራዊም ሆነ ክልላዊ የልማት ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም