በጅማ ዞን ከ92 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና ይወስዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዞን ከ92 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና ይወስዳሉ
ጅማ ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦በጅማ ዞን በ2018 ትምህርት ዘመን 92 ሺህ 545 ተማሪዎች ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና እንደሚወስዱ የዞኑ ትምህርት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
በዞኑ ለፈተናው አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉም ተመልክቷል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሚፍታሁ አብዱልቃድር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሳይንስ 11ሺህ 506 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 25 በመቶው በስምንት ማዕከላት ፈተናውን በኦንላይን የሚወስዱና ቀሪዎቹ ደግሞ በወረቀት እንደሚፈተኑ አቶ ሚፍታሁ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል 81ሺህ 39 ተማሪዎች የ8ኛ እና 6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የሚፈተኑ ይሆናል ብለዋል።
በዞኑ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከመደበኛው ሰዓት በተጨማሪ ትምህርት በመስጠት፣ አስፈላጊው ክትትል ሲደረግ መቆየቱን አመልክተዋል።
በኦንላይን ለሚፈተኑ ተማሪዎች ከወዲሁ አስፈላጊው ስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሠራቱን አስታውቀዋል።