የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የኃይል አቅርቦትን በማረጋገጥ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የኃይል አቅርቦትን በማረጋገጥ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር ያስችላል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የኃይል አቅርቦትን በማረጋገጥ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን እና መሠረተ-ልማት ዲቪዚዮን ዳይሬክተር ሮበርት ሊሲንጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን በሚያሳልጡ በትራንስፖርት፣ ኢንዱስትሪ፣ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች እና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ በትኩረት እየሰራች ነው፡፡
በዚህም በየዓመቱ ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ መቀነስና በታዳሽ ኃይል የሚመራ የትራንስፖርት ሥርዓት መገንባት የሚያስችል ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ስትራቴጂና የትግበራ ዕቅድ ይፋ አድርጋለች፡፡
በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ፣ኢኖቬሽን እና መሠረተ-ልማት ዲቪዚዮን ዳይሬክተር ሮበርት ሊሲንጌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ስትራቴጂ ከዓለም አቀፍ የህግ ማዕቀፎች ጋር የተናበበ ነው።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከውጭ የሚገባ ነዳጅ ጥገኛ በመሆናቸው ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጭ እንደሚዳረጉ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ስትራቴጂና የትግበራ ዕቅድ ወጭን ከመቀነስ ባሻገር ለአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ዋስትና ይሆናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እያደረገች ያለችው ሽግግር የአየር ብክለትን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ለሚደረገው ጥረት አጋዥ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር እስከ 2030 አዲስ ከሚመዘገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑትን በሀገር ውስጥ ለማምረትና ለመገጣጠም ማቀዷ በአፍሪካውያን መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ያጠናክራል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መጀመር ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረገውን ሽግግር ያሳልጣል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ በአህጉሪቱ ያለውን የንግድ እሴት ሰንሰለት እንደሚያቀላጥፍም ገልጸዋል፡፡