ቀጥታ፡

በክልሉ በከተሞች ከ200 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠሩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

ባህር ዳር፤ግንቦት 28/2018( ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በከተሞች ከ200 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠሩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ከተሞችን በኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ የማዘመን፣በቴክኖሎጂ የማላቅና ስማርት የማድረግ ስራ በሰፊው እየተካሄደ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፥ በክልሉ ከተሞችን ለኑሮና ኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ለዚህም በተለያዩ ከተሞች ከ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተሞቹ 1 ሺህ 10 የልማት ፕሮጀክቶች ተነድፈው በቅንጅት እየተተገበሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የልማት ፕሮጀክቶቹ በከተማ አስተዳደሮች በጀትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ግንባታቸው እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፥ በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከ200 ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች የስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል እስካሁን በተደረገ ጥረት 336 የሚሆኑት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰው፤ቀሪዎቹን እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእነዚሁ ፕሮጀክቶች መካከልም 14 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ፣ ከ40 በላይ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ድልድዮች፣ ከ80 በላይ ሼዶች እንዲሁም የኤሌክትሪክና የውሃ መስመር ዝርጋታና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራ የከተሞችን ሁለንተናዊ ገፅታ በመቀየር ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም