ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቀይ ባህር የዳር ተመልካች የምትሆንበት የቁጭት ጊዜ ሊያበቃ ይገባል-ምሁራን

ጎንደር፤ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የቀይ ባህር የጋራ ተጠቃሚ እንጂ የዳር ተመልካች የምትሆንበት የቁጭት ጊዜ ሊያበቃ ይገባል ሲሉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ የባህር በር ሳይኖራት ህልውናዋ ተጠብቆ መዝለቅ የማትችል በመሆኑ ምላሽ እስኪሰጣት የሁላችንም ጥያቄ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታልም ብለዋል።

ከቀይ ባህር በቅርብ እርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በመልክአ ምድርም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ የባህር በር ሊነፈጋት እንደማይገባ ይታመናል።

በዚሁ መሰረትም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ታምኖበት ለምላሹ የዲፕሎማሲ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ህጋዊ፣ፍትሃዊና ታሪክን መሰረት አድርጎ የቀረበው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያለበት የህልውና ጉዳይ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልጸዋል።

ከዩኒቨርሲቲው ምሁራን መካከል የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አንዳርጋቸው መስፍን፤የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት እንቆቅልሽ ሆኖ አመታት የተዳፈነ ጉዳይ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የሰፊ ህዝብና እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ያለ ባህር በር መኖር የማይቻላት መሆኑ እየታወቀ በዝምታ ብዙ አመታት ቢያልፉም አሁን ላይ የትውልድ ጥያቄ ሆኖ መጥቷል ብለዋል።

በመሆኑም ጥያቄው በታሪክ፣ በመልክአ ምድርም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ ተገቢ መሆኑን አንስተው፥ ምላሽ ሊሰጠው ግድ ይላል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ሳይኖራት ህልውናዋ ተጠብቆ መዝለቅ የማትችል በመሆኑ ምላሽ እስኪሰጣት የሁላችንም ጥያቄ ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ለጥያቄው ምላሽ ለመሻት በዲፕሎማሲው ረገድ የተጀመረ ጥረት የሀገርን ብሄራዊ ጥቅምና ክብር ያስቀደመ መሆኑን አንስተው፥ የኢትዮጵያን እውነት በማስረዳት ረገድ በተለይም ምሁራን ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናት ዳይሬክቶሬት የወቅታዊ ጉዳዮች ጥናት አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሀቢብ ሰይድ ፤ የባህር በር ጥያቄው ከብሄራዊ ጥቅም ባለፈ የሀገርና የዜጎች የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም በቀይ ባህር ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚ እንጂ የዳር ተመልካች የምትሆንበት የቁጭት ጊዜ ሊያበቃ ይገባል፤ ለዚህም በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት በአመክንዮ ላይ የተመሰረቱ ማስረጃዎችን በማቅረብና ለማስገንዘብ በተለይም ከምሁራን ብዙ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የስነ ጽሁፍ መምህር የሆኑት ገብሬ ሙሉዓለም (ዶ/ር)፤ በብርቱ የልማት ጥረት ስኬት የአባይ ትርክት እንደተቀየረ ሁሉ በቀይ ባህርም ላይ የኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት ትርክት መገንባት አለበት ብለዋል።

በዚህ ረገድ የዲፕሎማሲ ጥረቱ እንዳለ ሆኖ በተለይም የሀገራችን ምሁራን ዓለም ላይ ዘልቀው የሚገቡና ሚዛን የሚያስጠብቁ ፅሁፎችን በማሳተም የሀገራችንን እውነታ ማስረዳት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና እውነታን መሰረት ያደረገ ጥያቄ በመሆኑ የትውልዱ አጀንዳ ሆኖ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም