ባንኩ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ በማድረግ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማረጋገጥ አመርቂ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ በማድረግ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማረጋገጥ አመርቂ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ በማድረግ የደንበኞቹን ፍላጎት ከማረጋገጥ አንጻር አመርቂ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከቪዛ (Visa) ኩባንያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን አዲስ የግብይትና የክፍያ ካርድ አገልግሎት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፤ ባንኩ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም የባንኩ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሼባማይልስ (ShebaMiles) ደንበኞች በጋራ ሊጠቀሙበት የሚችሉትን የቅድመ ክፍያ ቪዛ ካርድ (CBE-ET Cobranded Visa Prepaid Card) ዛሬ ይፋ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ይህ አዲስ የቪዛ ካርድ የሼባማይልስ አባላት የኢ-ኮሜርስ ክፍያዎችን በቀላሉ መፈጸም የሚያስችላቸው ሲሆን፥ በሚያደርጉት ግብይትም የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ በር ይከፍታል ብለዋል።
ደንበኞች በካርዱ ግብይት በሚፈጽሙበት ወቅት የሼባማይልስ ነጥቦችን የሚያከማቹ ሲሆን፥ የተሰበሰቡትን ነጥቦች ለአውሮፕላን ትኬት መግዣና ለሌሎች የሼባማይልስ ማበረታቻ ጥቅማጥቅሞች ማዋል እንደሚችሉ አብራርተዋል።
የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው፤ የዚህ የቪዛ ካርድ ይፋ መሆን ለአየር መንገዱ የሼባማይልስ ደንበኞች ዘመናዊና የተቀላጠፈ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል።