ቀጥታ፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያና ሕዝቧ አሸናፊነት በተግባር የታየበት ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ አሸናፊነት በተግባር የታየበት መሆኑን ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት አስታወቀ።

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ምርጫው ስንሻው እንደገለጹት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያውያንን እውነተኛ ፍላጎት ያንጸባረቀና የሀገሪቷን ታሪካዊ ጠላቶች ቅስም የሰበረ ክስተት ነው።

ሕዝቡ ለሀገሩ ሰላምና ሉዓላዊነት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

ሀገርን ከጥፋት ጠብቆና ተቻችሎ መንግሥት የሚያቆመው ራሱ ሕዝቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘንድሮ ምርጫ እውነተኛው አሸናፊ ሕዝቡ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ምርጫው እንዳይሳካ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ከፍተኛ ጫናዎች ቢቃጡም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉንም ፈተናዎች በብስለትና በጽናት ተቋቁሞ መምረጡን ገልጸዋል።

ሕዝቡ ሰላም ወዳድ በመሆኑ ምርጫው በስኬትና በድል ሊጠናቀቅ መቻሉን የገለጹት ኃላፊው፤ ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊመሰገንና ሊደነቅ እንደሚገባው ተናግረዋል።

"ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት" ለሀገር ዘላቂ ሰላም የሚበጀው ሰላማዊ ትግል ብቻ ነው የሚለውን መርህ በመከተል ወደ ምርጫው መግባቱን የጠቀሱት ኃላፊው፤ በዚህም ፓርቲያቸው ከሕዝቡ ጋር በመሆን ታሪካዊ አሻራውን ማኖሩን አስገንዝበዋል።

የዘንድሮው ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ ታዛቢዎች ጭምር እውቅና ያገኘ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው አቶ ምርጫ፤ ለአብነትም የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እና ጃፓንን ጨምሮ በርካታ ሀገራትና ድርጅቶች የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡበትና ኢትዮጵያውያን መቻላቸውን ለዓለም ያሳዩበት አጋጣሚ እንደሆነ አብራርተዋል።

የምርጫው ሂደት ስኬታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅድመ-ምርጫና በምርጫ ወቅት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ያከናወናቸው ተግባራት ለውጤቱ መገኘት ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡

ለሂደቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የጸጥታ አካላት፣ ለሲቪል ማኅበራትና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ፓርቲው ያለውን ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም