ኢትዮጵያ ከአበረታች ቅመሞች ነጻ የሆነ ስፖርት ለመገንባት የጸና አቋም አላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከአበረታች ቅመሞች ነጻ የሆነ ስፖርት ለመገንባት የጸና አቋም አላት
አዳማ፤ ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን በመዋጋት ንጹህ ስፖርት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል ገለጹ።
ባለስልጣኑ በስፖርት ውስጥ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞች (Doping) እና ዘዴዎችን አስመልክቶ ለስፖርት ጋዜጠኞች ያዘጋጀው የስልጠናና የውይይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
ስልጠናው የተዘጋጀው ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጋር በመተባበር ነው።
የመድረኩ ዋና ዓላማ፥ ዶፒንግ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል ባለስልጣኑ ለጀመረው ስራ ስኬት የስፖርት ጋዜጠኞች የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል ነው።
አቶ መኮንን ይደርሳል ባለስልጣኑ ከቁጥጥር፣ ምርመራ እና ህጋዊ እርምጃ ባለፈ ሰፊ የንቅናቄ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና በተለይም ለስፖርተኞች ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞች በትምህርት ስርዓት ውስጥ መካተቱ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይና ይህም በዘላቂነት ንጹህ ስፖርትን ለመፍጠር እየተከናወነ ላለው ስራ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የስፖርት ፌዴሬሽኖች እና የስፖርት ስልጠና ማዕከላት የስልጠና ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለስፖርተኞች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።
ከምርመራ እና ቁጥጥር ጋር በተገናኘም የአበረታች ቅመሞች ተጋላጭነት ያለባቸው የስፖርት አይነቶችን በመለየት ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ ምርመራ ማድረግ የሚያስችል አቅም እንድትፈጥር የተጀመሩ ስራዎች በጥሩ መስመር ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው በቅርቡ የምርመራ ላቦራቶሪ ስራ ለማስጀመር እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
አበረታች ቅመሞችን የሚጸየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር እና የንጹህ ስፖርት እሳቤ እንዲሰርጽ በማድረግ ረገድ የሚዲያው ሚና ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ንዋይ ይመር ጋዜጠኞች በአበረታች ቅመሞች ዙሪያ ስነምግባርን ባከበረ መልኩ ዘገባዎችን ማቅረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ጋዜጠኞች በተከለከሉ አበረታች ቅመሞች እና በተፈጥሯዊ አቅም የሚገኙ ውጤቶች መካከል ያለውን ግልጽ ልዩነት ማወቅ እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።
አንድ ስፖርተኛ እስካልተረጋገጠ ድረስ ንጹህ የመሆን መብቱን (Presumption of Innocence) ጠብቆ መዘገብ እንዲሁም ታዳጊ ስፖርተኞች ህግና ስነ-ልቦናዊ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ መሆኑን ከግምት ማስገባት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
በአጠቃላይ ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነምግባርን አክብሮ በተከለከሉ የአበረታች ቅመሞች መከላከልና ቁጥጥር ላይ ኃላፊነት በተሞላበትና ብሔራዊ ፍላጎት ባማከለ መልኩ ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የስፖርት ጋዜጠኞች በበኩላቸው ስልጠናው ወቅቱን የጠበቀና የፀረ አበረታች ቅመሞች ስራዎች ላይ ግንዛቤ በማሳደግ ማህበረሰቡን ለማስተማር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።