ቀጥታ፡

በክልሉ ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ 

ሀዋሳ ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለፁ፡፡ 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ሀዋሳን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ጎብኝተዋል፡፡


 

ርእሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

በክልሉ የሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በይፋ ሥራ ከጀመረ በኋላ ባሉት ዘጠኝ ወራት ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ተገልጋዮች በማእከሉ  በተሰጣቸው አገልግሎት እርካታ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።    

አገልግሎቱን ወደ ሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ ስራ የጀመረውን የሀዋሳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለአብነት ጠቅሰዋል።


 

በሌሎች የክልሉ ከተሞችም አገልግሎቱን በማስፋት ህዝቡ ሳይንገላታ የተቀላጠፈ አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኝ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በግንባታ ላይ ያሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት የሚበቁ ማዕከላት መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

በሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመገኘት ከተገለገሉ ነዋሪዎች መካከል አቶ ወንደሰን አሸቴ፤በማዕከሉ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡


 

ወደ ማዕከሉ በመጡ በ30 ደቂቃ ውስጥ የሚፈልጉትን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

በማዕከሉ የአሻራ አገልግሎት እንዳገኙ የተናገሩት አቶ ፈጠነ አድማሱ በበኩላቸው በአጭር ጊዜ የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ጉዳያቸውን በጊዜ ጨርሰው ወደ ሌላ የዕለት ተግባራቸው መሄድ እንደቻሉም አስረድተዋል፡፡


 

በአጭር ጊዜ ውስጥ ግልፅና የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘት መቻሉ በራሱ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው የሲዳማና የሀዋሳ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ማዕከላትን እንዲሁም በወንዶ ገነትና ለኩ ከተሞች እየተገነቡ ያሉ ማዕከላትን የተመለከቱ ሲሆን ሌሎች የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም