ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቅድሚያ ለጎረቤት የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት መፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቅድሚያ ለጎረቤት የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት መፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለዓለም አቀፍ ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ፣ የኃያልነት ፍትጊያ ማዕከልና ያልተነኩ ሃብቶች ወደ አሏቸው የአፍሪካ ሀገራት ዋና መግቢያ በር ሆኖ ያገለግላል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ቀንድ ዓለም አቀፍ ፍላጎትና ተግዳሮት የሚንፀባረቅበት ስትራቲጂክ ቀጣና ነው።

ለአብነትም አሜሪካ፣ ቻይና፣ የአውሮፓና የመካከለኛው ምስራቅ የባሕረ ሰላጤ ሀገራት ስትራቴጂክ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የትኩረት ማዕከላቸው ማሰሪያ አድርገው እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።

በሌላ መልኩም የሽብር ኃይሎች ደካማ የመንግሥት መዋቅሮችንና ድንበሮችን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ትኩረት ለመሳብና የኢኮኖሚ ምንጭ ለማግኘት መሞከራቸው የቀጣናው ሁነኛ ስጋት አድርጓቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያም ቅድሚያ ለጎረቤት በሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በኢኮኖሚ ትስስር እንዲሁም በሰላምና ደኅንነት ዘርፍ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን አንስተዋል።

ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባሻገርም የተጋመደውን የቀጣናው ህዝብ በኃይል እና በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ለቀጣናዊና አህጉራዊ የንግድ ስምምነት ትግበራ መሪ ሚናዋን እየተወጣች እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በትራንስፖርትና በዲጂታል መሰረተ ልማት፣ በወደብና የባሕር በር አማራጭ የማስፋት ስራ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ውጤታማ አካሄድ እየተከተለች መሆኑን አስረድተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የሽብር ኃይሎችን ህልም በማምከን የምታበረክተው ጉልህ አስተዋጽኦም ለሁለትዮሽና ባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ውጤታማነት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ ከውጤታማ ዲፕሎማሲ ጋር በማጣጣም የባሕር በር ባለቤትነትና የማሪታይም ስትራቴጂን ማረጋገጥ እንዳለባት አስረድተዋል።

ለዚህም ከቀጣናው ሀገራትና ኃያላኑ ጋር ስትራቴጂክ አጋርነትን በማጎልበት የህዝብ ለህዝብ መስተጋብርና ስብጥርን በትልቅ የዲፕሎማሲ መሳሪያነት መጠቀም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያን የጎረቤት ሀገራት የብልጽግና ዋስትናነት የሚያጎላ የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ስትራቴጂ ቀርጾ መተግበር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ኮሌጅ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር አየለ በከሪ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሕዝቦች በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በባሕል የጋራ ዕሴቶች የተጋመዱ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና የልማት ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ ኢኮኖሚ ውህደትን ለማፋጠን የምታደርገው ውጤታማ ጥረት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ቅቡልነት በማሳደግ የተፅዕኖ ፈጣሪነት አቅሟን ማጎልበት ያስቻለ ስኬት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የምስራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት በማፋጠን፣ የውስጥና ቀጣናዊ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን በማስከበር ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎቷን ማረጋገጥ እንደሚኖርባት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም