ቀጥታ፡

ከተለያዩ ሀገራት ጋር የተደረጉት ስምምነቶች የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የአየር መንገዱን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የተደረጉት ስምምነቶች የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ መሆናቸውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 23ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር)፤ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የተደረጉት ስምምነቶች የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እና የአየር መንገዱን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን ሪፐብሊክ፣ ከአንጎላ ሪፐብሊክ፣ ከባንግላዲሽ ሕዝባዊ ሪፐብሊክ እና ከኢስዋቲኒ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጋር ያደረገቻቸውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ ሪፖርቶችና የውሳኔ ሃሳቦችን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

እነዚህ የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆች ለንግድና ኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም፣ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንዲሁም የአየር ትራንስፖርት መዳረሻዎችን ለማስፋፋት ያላቸውን ከፍተኛ ጠቀሜታ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ስምምነቶቹ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁና በዘርፉ ያላትን ሚና በማጉላት ተጠቃሚነቷን የሚያሳድጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ምክር ቤቱም በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ አዋጆቹን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ከምክር ቤቱ አባላት በኩልም የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆቹ የአየር መንገዱን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል፣ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል የጋራ የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የተፈረመው ስምምነት ረቂቅ አዋጅም በምክር ቤቱ ጸድቋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር)፤ ስምምነቱ የሀገሪቱን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን፣ ለዓሳ ሀብት ልማት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማሳደግና በዘርፉ የግል ባለሀብቶችን ለመሳብ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማትን አቅም ለማሳደግና የምርምር ሥራዎችን ወደ ገበያ አውጥቶ ለማቅረብ ያለውን ጠቀሜታም አንስተዋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሻል የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ ዜጎች ቪዛን ለማስቀረት በተፈረመው የስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ፣ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም