መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን የዜጎችን እንግልት እያስቀረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን የዜጎችን እንግልት እያስቀረ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን የዜጎችን እንግልት እያስቀረ መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የተገነባውን መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት መርቀው ከፍተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ የመንግሥት አገልግሎቶችን ፍትሀዊነት የሚያረጋግጥ ቀልጣፋና ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ ምኅዳር እየተፈጠረ ነው።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ህብረተሰቡ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያጋጥመውን የመልካም አስተዳደር ችግር በማስቀረት አዎንታዊ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትንም ከአንድ ማዕከል ወደ ተንቀሳቃሽ በማሸጋገር የተደራሽነት አድማሱን የማስፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ከተማ አስተዳደሩ የአዲስ አበባን የመንግሥት አገልግሎቶች ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የወሰደውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አስረድተዋል።
ለምረቃ የበቃው የኮልፌ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ለህብረተሰቡ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት በሚያስችል መልኩ የተገነባ መሆኑን አብራርተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን እንግልት እያስቀረ ያለ ውጤታማ ስራ ነው ብለዋል።
በዚህም በመዲናዋ የመሶብ አንድ ማዕከላት ተደራሽነትን በማስፋትና የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን የመፈፀም ውጤታማነትን እያሻሻለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ ወልደ ሚካኤል፤ የኮልፌ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የክፍለ ከተማውን አገልግሎቶች ለማሳለጥ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።