ቀጥታ፡

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ሰላምና ደኅንነት አፈፃፀም ገመገመ

‎አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2018(ኢዜአ)፦ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፀጥታና ደኅንነት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ተገምግሟል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የጋራ ግብረ ኃይሉ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫው ወቅትና ከምርጫ በኋላ ያሉ ስራዎችን እንደ ሀገር ዕቅድ አውጥቶ በቅንጅት በመመራቱ፤ በተግባር የተፈተሸ፣ የተናበበና ሰላምን ለማፅናት ጀግንነት የታየበት ተግባር በመፈፀሙ ምርጫው በሰላም ሊጠናቀቅ ችሏል ብለዋል።


 

ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ በተሰራው ሪፎርም አሁን ላይ በተጨባጭ ትላልቅ ተልዕኮዎችን መሸከም የሚችሉ የፀጥታ ተቋማት መፈጠራቸውን በምርጫው ላይ የተመዘገበው ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል።

የጋራ ግብረ-ኃይሉ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ በሀገር ውስጥና በውጭ ጠላቶች የተቀናጀውን ከፍተኛ ሴራ ያከሸፈ፣ ያመከነና የሀገርን ሉዓላዊነት ያረጋገጠ፤ የሪፎርሙ ውጤት በተግባር የተለካበትና የታየበት መሆኑንም ገልፀዋል።

እንደ ፀጥታ ተቋም መኩራትና መመካት ያለብን በኢትዮጵያ ህዝብ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል በሀገራችን ላይ እየሆነ ያለውን ተረድቶ፣ ሁሉንም በሚዛን አስቀምጦ፣ የምርጫው ቀን ሲደርስ ለሁላችንም ትምህርት ያስተላለፈ የሀገር አንድነት እና ሉአላዊነትን ያጸና የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ህዝብ መሆኑን ያረጋገጠበት እንዲሁም ከዚህ በኋላ መንግስት በካርድ እንጂ በጥይት አይሆንም የሚል መልዕክት ያስተላለፈበት ምርጫ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በቀጣይም በሽብርተኞችና በፅንፈኞች ላይ የተጀመረው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፀው የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ፤ የምርጫው ውጤት ታውቆ አዲስ የመንግስት ምስረታ እስከሚከናወን እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ያሉ ሕዝባዊና መንግስታዊ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የፀጥታ ሥራው ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም