ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች ለአቅመ ደካማ ወገኖች አስረከበ

አምቦ፤ ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ)፦ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሃጫሉ ሁንዴሳ ካምፓስ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስገነባቸውን የመኖሪያ ቤቶች ለአቅመ ደካማ ወገኖች አስረከበ።

ዩኒቨርሲቲው ቤቶቹን በ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ማስገንባቱንም የቤቶቹ ርክክብ በሚከናወንበት ወቅት ተገልጿል።


 

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሃጫሉ ሁንዴሳ ካምፓስ ዲን ኢንጂነር ወዬሳ አራርሳ በወቅቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት አቅም የሌላቸው ወገኖችን በበጎ ፈቃድ ተግባራት ተጠቃሚ እያደረገ ነው።


 

በዚህም ዩኒቨርሲቲው በበጎፈቃድ ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች ለአቅመ ደካማ ወገኖች ዛሬ አስረክቧል ብለዋል።

ለቤቶቹ ግንባታም ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና መምህራን እንዲሁም ከተማሪዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መዋጮ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት እንደሚተጋም አረጋግጠዋል።

በከተማዋ የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ማህበራዊ ችግሮች እንዲቃለሉ ማገዛቸውን ያነሱት ደግሞ የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃጫሉ ገመቹ ናቸው።


 

የበጎ ፈቃድ ተግባራቱ ለተቸገሩ ወገኖች ለመድረስ እንዳስቻሉ ገልጸው፤ የሕብረተሰቡ የእርስ በርስ የመተጋገዝ እሴት እንዲጎለብትም አድርገዋል ብለዋል።

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ሴቶች እና ሕፃናት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢሊሌ ተስፋዬ በበኩላቸው የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በከተማዋ በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ለአቅመ ደካማ እናቶች ቤት ሰርቶ ከማስረከብ ባሻገር ለተቸገሩ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡


 

የመኖሪያ ቤት ከተረከቡ ነዋሪዎች መካከል ሶስት ልጆቻቸውን ይዘው ደሳሳ ቤት ተከራይተው ይኖሩ የነበሩት ወይዘሮ አዳነች ጭምሳ ይገኙበታል።

ተከራይተው የሚኖሩበት ቤት የሚያፈስ በመሆኑ በክረምት ወቅት ለመኖር አስቸጋሪ ጊዜን ማሳለፋቸውን ተናግረው አሁን ዩኒቨርሲቲው የቤት ባለቤት ስላደረጋቸው ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።


 

ወይዘሮ ብርሃኔ ገመቹ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም አምስት ልጆቻቸውን ይዘው ጎዳና ላይ ይኖሩ እንደነበር ጠቁመው የተረከቡት ቤት ይህንን ችግር እንዳስወገደላቸው ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እሳቸውን ከችግር እንዳወጣቸው ሁሉ ለሌሎች ለተቸገሩ ወገኖች እንዲደርስም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም