ቀጥታ፡

የምርጫ ሂደቱ እውነተኛ ዴሞክራሲ በተግባር ፀንቶ የታየበት ነው- የጋራ ምክር ቤቱ

ጋምቤላ፤ ግንቦት 27/2018 (ኢዜአ)፡- የምርጫ ሂደቱ  ቅቡልነት ያለውና እውነተኛ ዴሞክራሲ በተግባር ጸንቶ የታየበት መሆኑን በጋምቤላ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 7ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢና የኢዜማ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ኮማንደር ጋትቤል ቦል፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁን  ገልጸዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች የነገውን የክልሉንና የሀገሪቱን እጣ ፈንታ ለመወሰን በምርጫው ዕለት ከጧቱ 12:00 ስዓት ጀምሮ በነቂስ በመውጣት ለምርጫው ስኬታማነት ያሳዩት ተሳትፎ በእጅጉ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የምርጫው ሂደትም እጅግ የተረጋጋ፣ ፍጹም ሰላማዊና የክልሉንና የሀገሪቷን መጻኢ የዴሞክራሲ ትግበራን በተግባር አጠናክሮ ያለፈ መሆኑን ገልጸዋል። 

በክልሉ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ የነበረው ሂደት ፍጹም ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት ላሳየው ቁርጠኝነትም ምክር ቤቱ ምስጋና ያቀርባል ብለዋል።

ህዝብ የሰጠው ድምጽ የመጨረሻው የስልጣን ባለቤትነት መገለጫ በመሆኑ በቦርዱ የሚገለፀውን የምርጫ ውጤት በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነም የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ገልጸዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢና የህዳሴ ፓርቲ የጋምቤላ ክልል አስተባባሪ መምህር ሻምበል ቶላ በበኩላቸው የምርጫው ሂደት ፍጹም ፍትሐዊ፣ ታዓማኒና ሰላማዊ እንደነበር ገልጸዋል።

በምርጫው ህዝቡ በነፃነትና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ላመነውና ይበጀኛል ለሚለው የፓለቲካ ፓርቲ ድምጹን መስጠቱን ጠቁመው፤ ሚዲያዎችም ገለልተኛ ሆነው ለምርጫው ስኬታማነት ለሰጡት ሽፋን ምስጋና ይገባል ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ጸሐፊና በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፔን ኡጁሉ የዘንድሮው ምርጫ በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለውና እውነተኛ ዴሞክራሲ ጸንቶ የታየበት እንደነበር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም